በትራንስፎርሜሽን ትግበራ ንቅናቄ ላይ የተዘጋጀ መድረክ ተካሄደ

    የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የትራንስፎርሜሽን ትግበራ ንቅናቄ ላይ የተዘጋጀ መድረክ ሐምሌ 15/ 2017 ዓ.ም አካሄደ። ኮርፖሬሽኑ ባዘጋጃቸው የሥልጠና ሰነዶች ማለትም የገበያ ስልት (ማርኬቲንግ ስትራቴጂ)፣ ተቋማዊ ማህበራዊ ኃላፊነት፣ የዋጋ ግንባታ ስልት፣ የሥራ ፍሰት አስፈላጊነትና ትግበራ (SOP) እና ተያያዥ ሰነዶች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ለዘርፍ አማካሪዎች፣ ለዳይሬክተሮች፣ ለዋና ክፍል ኃላፊዎችና ለሚመለከታቸው ፈጻሚዎች ተሰጥቷል፡፡

    መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኃይሉ ንጉሴ ባስተላለፉት መልእክት ኮርፖሬሽኑ በለውጥ ሂደት ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው የኮርፖሬሽኑ ተቆጣጣሪ የሆነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የትራንስፎርሜሽን አማካሪዎች መድቦ የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ትላንት የነበሩ ጠንካራ አሰራሮችን በማስቀጠልና ደካማዎቹን በማስቀረት ዘመናዊ አሰራርን ማስፈን እንደሚገባ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡ በተለይም ተቋሙን ሲፈትኑ የነበሩ አሰራሮችን ሊያስተካክሉ የሚችሉ የአሰራር ሰነዶች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው በተያዘው በጀት ዓመት በእቅድ የተያዙ የግዢና ሽያጭ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ መሰራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

    በመድረኩ በገበያ ስልት በማህበራዊ ኃላፊነት እና በዋጋ ግንባታ ስልት ላይ የተዘጋጁ ሰነዶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የትራንስፎርሜሽን አማካሪዎች በሆኑት በአቶ ተሻለ በልሁ እና ወ/ሮ ኤደን ፈንታ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

    በተመሳሳይ የሥራ ፍሰት (SOP) አስፈላጊነትና ትግበራ እና የትራንስፎርሜሽን ቡድን አሰራር ሰነድ በለውጥና አሠራር ማሻሻያ ዳይሬክተር ትእዛዙ ኃ/ጊዮርጊስ የቀረበ ሲሆን የግዢ፣ የሽያጭ፣ የኢንቨንተሪ እና የገቢና ወጪ ንግድ የሥራ ፍሰት በኮርፖሬሽኑ ባለሙያዎች ቀርበው አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል።