በኮርፖሬሽኑ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

በኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚና የዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈጻሚዎች፣ የዘርፍ አማካሪዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ የዋና ክፍል እና የክፍል ኃላፊዎች በተገኙበት ነሐሴ 2/ 2017 ዓ.ም ተካሄደ፡፡

በመድረኩ የዘርፎችና ዳይሬክቶሬቶች የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን አፈጻጸሙ በጥቅሉ አበረታች እንደነበር እና ለአዲሱ በጀት አመት ተስፋ ሰጪ ውጤት የታየበት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ በኃይሉ ንጉሴ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጥሩ ደረጃ ላይ የነበሩ ሥራዎችን የማስቀጠል፤ ችግር ያለባቸውን አሰራሮች ደግሞ የማስተካከል ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በተለይም ምርትን ገዝቶ ከማከማቸት ባለፈ በብዛት መሸጥ ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ በተያያዘም በወጪ ንግድ የነበረውን አፈጻጸም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባና የገቢ ንግድ ላይ ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኮርፖሬሽኑ 909,847 ኩንታል ምርት ግዢ ያከናወነ ሲሆን 1,260,061 ኩንታል ምርት በሃገር ውስጥና በውጪ ገበያ ሽያጭ አከናውኗል፡፡ እንዲሁም ኮርፖሬሽኑ የተሽከርካሪ ጥገና፣ የምድር ሚዛን፣ የእህል እጥነት፣ የጭነት፣ የማበጠር እንዲሁም የስልጠናና ማማከር አገልግሎት ለደንበኞች ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል የኮርፖሬሽኑ የ2018 በጀት ዓመት እቅድ የቀረበ ሲሆን እቅዱ አሁናዊ አለማቀፋዊና ሃገራዊ ሁኔታዎችን እንዲሁም ባለፉት ዓመታት የነበሩ ጥንካሬዎችና ድክመቶችን በመተንተን መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ የወጪ ንግድን ማጠናከር፣ የገቢ ምርቶች አቅርቦት ሰንሰለትን ማሳደግ፣ የሃገር ውስጥ የምርት አቅርቦት ትስስርን ማጠናከር፣ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን መተግበር፣ ዲጂታላይዜሽንን መተግበር፣ ዘመናዊ የአትክልና ፍራፍሬ ምርት ማቀዝቀዣና ማቆያ (ኮልድ ስቶር) ሥራ ላይ ማዋል፣ ምርትን በጥሬው ከመሸጥ ባለፈ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎትን ማሻሻል እና ዘመናዊ የግብይት መዳረሻዎችን ማስፋት ኮርፖሬሽኑ በ2018 በጀት ዓመት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

በቀረበው የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ላይ በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተሰንዝረው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡