
የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አመራርና ሰራተኞች በ2018 በጀት ዓመት ሃገራዊ የልማት እቅድ ዙሪያ ሐምሌ 17/ 2017 ዓ.ም ውይይት አደረጉ።
በኮርፖሬሽኑ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ ም/ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ዱባለ የሃገራዊ እቅድ ሰነዱን ያቀረቡ ሲሆን በሃገር ደረጃ የተዘጋጀውን እቅድ እንድናውቀው መደረጉ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው 2017 በጀት ዓመት በበርካታ የልማት ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች የተመዘገበበት እንደነበር ገልጸዋል። በሰነዱ ከተካተቱት መካከል አለም አቀፍ የኢኮኖሚ አዝማሚያ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ እቅድ፣ የኢኮኖሚ ዘርፎች እቅድ፣ የማህበራዊ ዘርፎች እቅድና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
በ2017 ከፍተኛ አፈጻጸም የታየበትን የቡናና ወርቅ ወጪ ንግድ በተያዘውም ዓመት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገልጿል። በተለይም በ2017 በጀት ዓመት 8.8 በመቶ ሃገራዊ እድገት መመዝገቡና በ2018 በጀት ዓመት 9 በመቶ እድገት እንደሚጠበቅ ተመልክቷል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኃይሉ ንጉሴ የውይይት መድረኩን ሲመሩ ባስተላለፉት መልዕክት የቀረበው ሃገራዊ እቅድ “ለኛ ተቋም ምን ማለት ነው?” የሚለውን ወስዶ ማየትና የተቋሙን እቅድ ከዚህ አንጻር መገምገም ይገባል ብለዋል። አያይዘውም የገቢ መሰብሰብ አቅምን ማዳበር፣ ውጤታማ የፋይናንስ አስተዳደር፣ የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር፣ የንግድ መዳረሻን ማስፋትና ዲጂታላይዜሽን የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ከሆኑት ዋነኞቹ እንደሆኑ በመጥቀስ ለተግባራዊነቱ ተቋማዊ ድርሻን መወጣት እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።
የቀረበውን ሰነድ ተከትሎ አመራርና ሰራተኞች ያሏቸውን ጥያቄዎችና አስተያየቶች አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
