ኮርፖሬሽኑ የክረምት የበጎ አድራጎት ተግባራት አከናወነ

    የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በክረምት የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ በማከናወን ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

    የኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት ከድሬዳዋ ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር በመቀናጀት የደም ልገሳ፣ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና የቤት እድሳት ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።

    የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኃይሉ ንጉሴ የኮርፖሬሽኑ የአትክልትና ፍራፍሬ እና የእህልና ቡና ምርት አቅርቦት በድሬዳዋ ማህበረሰብ በደንብ እንደሚታወቅና ተቋሙና ማህበረሰቡ ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው መሆኑን በመግለጽ ማህበረሰቡን በማገልገላቸው ደስ እንደሚሰኙ ተናግረዋል። የድሬዳዋ አስተዳደርም ላደረገው የሞቀ አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    ኮርፖሬሽኑ ለ2018 የትምህርት ዘመን በድሬዳዋ አስተዳደር ስር ለሚገኙ ከ1 መቶ 80 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ተማሪዎች 182 ደርዘን ደብተርና 88 ካርቶን እስኪቢርቶ ድጋፍ አደርጓል። ይህ ድጋፍ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑ ተመልክቷል። ድጋፉንም የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኃይሉ ንጉሴ ለድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ተወካይና የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ለአቶ አሚኖ ጣሀ አስረክበዋል።

    አቶ አሚኖ ጣሀ በርክክቡ ወቅት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ያደረገው ድጋፍ የማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻር የተከናወነ ሲሆን፣ በቀጣይም ተመሳሳይ ድጋፎችን እንደሚያደርግ እንጠብቃለን በማለት ድጋፉ ኮርፖሬሽኑ በንግድ ሥራዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ተሳትፎ ያሳያል ብለዋል። ድጋፉንም በመረከብ ለአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ አስረክበዋል።

    የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ተወካይ የሆኑት አቶ አብዱልፈታ መሀመድ በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ በቢሮው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
    በተጨማሪም የመኖሪያ ቤታቸው እድሳት ለሚያስፈልገው አቅመ ደካማ አረጋዊያን የቤት እድሳት የማስጀመር ተግባር ተከናውኗል። የቤት እድሳቱ ተጠቃሚዎች ለተደረገላቸው ድጋፍ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል።