ኮርፖሬሽኑ እና በኢንተርፕራይዙ መካከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

በኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና በአዲስ አበባ የንግድ ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ መካከል የመግባቢያ ስምምነት ጥር 08 ቀን 2018 ዓ.ም ተፈረመ፡፡

የስምምነት ሰነዱን የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኃይሉ ንጉሴ እና የአዲስ አበባ የንግድ ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ መሥፍን አሰፋ ተፈራርመዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኃይሉ ንጉሴ ሁለቱ ተቋማት ራሳቸውን ችለው የተቋቋሙ ቢሆንም በጋራ መሥራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው ለመሥራት የጋራ ስምምነቱ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹ ሲሆን የአዲስ አበባ የንግድ ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ መሥፍን አሰፋ በበኩላቸው ተባብረን መሥራታችን ከምንም በላይ ለሃገር ይጠቅማል በማለት ስምምነቱ እውን እንዲሆን ኮርፖሬሽኑ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የስምምነት ሰነዱ ዓላማ በተለያዩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ግዥ እና ሽያጭ ላይ በጋራ ለመስራት፣ የልምድ እና የተሞክሮ ልውውጥ ለማድረግ፣ በጋራ ውጤታማ ተቋም ለመገንባት፣ የገበያ መረጃ ልውውጥ ለማጠናከር እንዲሁም በጋራ የመስራት ባህልን ለማዳበር ነው።