የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ፖስታ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ፖስታ ያሏቸውን የግብይት እና የሎጀስቲክስ ሰንሰለት በማቀናጀት በኢ-ኮሜርስ ዲጂታል የግብይት ማዕቀፍ ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መጋቢት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ተፈራርመዋል።

የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱን የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ በኃይሉ ንጉሴ እና የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳግማዊ ኃይልዬ የተፈራረሙ ሲሆን ስምምነቱ ኮርፖሬሽኑ የሚያቀርባቸውን የእህል፣ የአትክልት እና የፍራፍሬ ምርቶች ለህብረተሰቡ በስፋት ለማድረስ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ በኃይሉ ንጉሴ በፊርማው ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንደገለጹት ይህ ስምምነት ምርቶችን በቀጥታ ከአምራቹ ወደ ሸማቹ በማድረስ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጡም በላይ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል። አክለውም ሁለቱ ተቋማት ያሏቸውን ትልልቅ እሴቶች በጋራ ለመጠቀም ስምምነቱ እንደ መነሻ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳግማዊ ኃይልዬ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፖስታ ያለውን ግዙፍ የሎጀስቲክስ አቅም፣ የትራንስፖርት መሰረተልማት እና በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ቅርንጫፎቹን ተደራሽነት በመጠቀም ምርቶቹ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ዜጎች እንዲቀርቡ እንደሚደረግ ገልፀዋል። አያይዘውም የኢ-ኮሜርስ ዲጂታል የግብይት ማዕቀፍን ትኩረት ሰጥተው እየሰሩበት እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡