አመሠራረት
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢንሥኮ)የኢ/ፌ/ዴ/ሪ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 916/2008 አንቀጽ 5 እና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 25/1984 አንቀጽ 47(1) መሠረት ታኅሣስ 12 ቀን 2008 ዓ/ም የተቋቋመና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር የሚተዳደር የፌዴራል መንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ መሠረታዊ የምግብ ምርቶችንና ልዩ ልዩ የፍጆታ ሸቀጦችን ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብና በማሠራጨት የሀገር ውስጥ ገበያን የማረጋጋት እንዲሁም በግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሣደግ የሚሠራና በ2022 ተመራጭ የልማት ድርጅት ሆኖ የመገኘት ራዕይን የይዞ የሚንቀሳቀስ የልማት ተቋም ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ የተቋቋመባቸው ዓላማዎች
- የተመረጡ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችንና፣ መሠረታዊ ሸቀጦችን ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር በተወዳዳሪ ዋጋ ገዝቶ በማሰራጨት የአገር ውስጥ ገበያን ማረጋጋት፤
- ሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ በተመረጠ አኳኋን ማስመረት፣ መግዛትና ማሰራጨት፤ ክምችት መያዝ፣ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ማቅረብ፤
- የአርሶ አደሩ የማምረት ፍላጎት እንዲያድግ ለግብርና ምርቶች አስተማማኝ ገበያ እንዲፈጠር እገዛ ማድረግ፤
- ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ኃላፊነት እና ተጠያቂነት የሰፈነበት የግብይት አሠራር መዘርጋትና መፈፀም፤
- ለሥራው የሚፈለገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በሚፈለገው ዓይነት፣ መጠንና ጥራት ለማፍራት እንዲቻል ከሚመለከታቸው የምርምር፣ የትምህርትና የሥልጠና ተቋማት ጋር መተባበር፤
- በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ተወዳዳሪና አትራፊ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ እገዛ የሚያደርጉለትን የሰው ኃብት፣ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና የዘመናዊ ሥራ አመራር ግብዓቶችን ለማግኘት የሚያስችለውን ኢንቨስትመንት መሳብም ሆነ በኢንቨስትመንት ላይ መሳተፍን ጨምሮ ጥናት በማካሄድ ሲፈቀድ ተግባራዊ ማድረግ፤
- ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተዛማጅ ተግባሮችን መፈጸም፡፡
