
ስለ ኢንሥኮ
የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 916/2008 አንቀጽ 5 መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 369/2008 ታኅሳስ 12 ቀን 2008 ዓ/ም የተቋቋመ የፌዴራል መንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በተናጠል ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን የኢትዮጵያ የእህል ንግድ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ አክስዮን ማህበር እና የግዥ አገልግሎት ድርጅትን በማቀፍ በንግዱ ዘርፍ ከተሠማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በተመሠረተ መደጋገፍና መተባበር በመሥራት የንግድ ግብይት ሥርዓቱን የተረጋጋ፣ ዘመናዊ፣ አስተማማኝና ውጤታማ ለማድረግና ተወዳዳሪ ተቋም ሆኖ ለመገኘት የሚሠራ የመንግሥት የልማት ተቋም ነው፡፡

የዋና ሥራ አስፈጻሚው መልዕክት
እንኳን ወደ ኢንሥኮ ድረገጽ በደኅና መጡ!
የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአገራችንን የንግድ ሥርዓት ለአገራዊ ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት የተሻለ አስተዋጽዖ ማድረግ በሚችልበት ደረጃ ላይ ለማድረስ በተወሰዱ ርምጃዎች አካልነት በ2008 ዓ/ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 369/2008 እና የልማት ደርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/1984 መሠረት የቀድሞዎቹን የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ አክስዮን ማህበርና የግዢ አገልግሎት ድርጅትን በማዋሃድ የተቋቋመ ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ ቀደም ሲል በተናጥል ሲካሄዱ የነበሩ የምርትና አገልግሎት ንግድ ሥራዎችን ውጤታማነትና አገራዊ ፋይዳ የሚያጎለብቱ የአሠራርና አደረጃጀት ማሻሻያዎችን በየጊዜው ተግባራዊ በማድረግ ራዕዩ አድርጎ ለተነሳው ገበያን በማረጋጋትና የውጭ ምንዛሪ ገቢን በማስገኘት በ2022 ተመራጭ የንግድ ተቋም ሆኖ የመታየት ትልም በትጋት እየሠራ ይገኛል፡፡



