photo_2024-08-26_09-36-41_2.jpg

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባዘጋጀውና ከነሐሴ 19-23/ 2016 ዓ.ም በሚቆየው "የኢትዮጵያን ይግዙ" የንግድ ሳምንት ላይ ምርትና አገልግሎቱን ለጎብኚዎች አስተዋውቋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለሃገር ውስጥና ለውጪ ገበያ የሚያቀርባቸውን የተለያዩ የእህል፣ የቡና፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እና የፍጆታ እቃዎች ለተጠቃሚዎች ማቅረቡ ምርቶቹን ለማስተዋወቅና ተደራሽነቱን ለማስፋት የጎላ ፋይዳ ያለው ሲሆን በዘርፉ ከተሰማሩ አካላት ጋር የንግድ ትስስርና ግንኙነት ለመፍጠር ያስችላል፡፡

በንግድ ሳምንቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ካሳሁን ጎፌ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን የሃገራችን ምርት በሰፊው የሚታይበትና መላው ህብረተሰብ የሚሳተፍበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የንግድ ሳምንቱ ነሐሴ 19/ 2016 ዓ.ም በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀው ቦታ ክቡራን ሚኒስቴሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ አምባሳደሮች፣ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮችና የተለያዩ የሥራ አመራሮች በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል፡፡ በተያያዘም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ያዘጋጀው የወጪ ንግድ ቋሚ የኤግዚቢሽን ማእከል ተመርቋል፡፡