የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከኩሽላደር ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ጋር የህንጻ ሙሉ እድሳት (ሪኖቬሽን) የውል ስምምነት ግንቦት 15 ቀን 2016 ዓ/ም አደረገ፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ እና የህንጻ እድሳት የሚያከናውነው የኩሽላደር ኮንስትራክሽን ጄነራል ማናጀር አቶ አዲሱ ሞሲሳ የውል ስምምነት ፊርማውን ያከናወኑ ሲሆን ስምምነቱ የዋና መ/ቤት ብሎክ ሁለት ህንጻን ሙሉ እድሳት ለማድረግ የተካሄደ ነው፡፡
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ የህንጻ እድሳቱ ዋና ምክንያት መጪውን ጊዜ የሚመጥን የቢሮ አደረጃጀት እንዲኖርና ለሥራ ምቹ የሆነን ከባቢ ለመፍጠር መሆኑን ጠቁመው፤ የህንጻ እድሳት የሚያከናውነው ድርጅት በጥራትና በጊዜ ስራውን እንዲያከናውን አሳስበዋል፡፡
የኩሽላደር ኮንስትራክሽን ጄነራል ማናጀር አቶ አዲሱ ሞሲሳ በበኩላቸው ድርጅታቸው ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ፈጽሞ የማስረከብ ልምድ እንዳለው ገልጸው፤ የስራ ብቃታቸውን በማሳየት ሌሎች ፕሮጀክቶችንም ከኮርፖሬሽኑ ጋር መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
የህንጻ እድሳቱ በሶስት ምእራፍ የሚከናወን ሲሆን የመጀመሪያው ምእራፍ ከ20 ቀናት በኋላ እንደሚጀመር ይጠበቃል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽንን ያለፉት ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ጥር 8/ 2016 ዓ.ም በአካል ተገኝተው ግምገማ አካሄዱ፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዱ የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የፍጆታ ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት አበረታች ስራዎችን ስለመሰራቱ ጠቁመው፤ ነገር ግን የአፈጻጸም ጉድለት ያለባቸውን በስፋት አቅዶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል::
የኢትዮጰያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቻ ደምሴ የቋሚ ኮሚቴው አባላትን በአከል ተገኝተው ግምገማ በማድረጋቸው አመስግነው፤ በኮሚቴው እየተደረገ ያለው ድጋፍ ጥሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር እና ህገ ወጥ የንግድ ስርአት ለተቋሙ ተግዳሮት እንደሆነ ተናግረው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙት የተቋሙ ይዞታዎች ከህግ አግባብ ውጪ እየተወረሰ በመሆኑ የተቋሙ ህልውና አደጋ ላይ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚው አስረድተዋል።
ኮርፖሬሽኑ ባለፉት 6 ወራት ካቀረባቸው የሽያጭ ምርቶች ከመደበኛው የግብይት ዋጋ በጠቅላላው 1.3 ቢሊዮን ብር ተቀናሽ በማድረግ በገበያ ማረጋጋቱ ስራ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከቱን በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት የኮርፖሬሽኑን ያለፉት ስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸምን ከመገምገም ባለፈ ከኮርፖሬሽኑ መሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም ቃሊቲ የሚገኙትን የፍጆታ እቃዎች ንግድ ስራ ዘርፍ መደብርና የቡና ማእከል፣ ሳሪስ የሚገኘውን የእህል ማከማቻና ማደራጃ ማእከል እንዲሁም የኮርፖሬት ሎጀስቲክስና ቴክኒክ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የስራ እንቅስቃሴ ከጎበኙ በኋላ ግብረ መልስ ሰጥተዋል::
በማጠቃለያው የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዱ ከኮርፖሬሽኑ ተልእኮ ጀምሮ ግልጽነት ስለመፈጠሩና ተቋሙን በደንብ እንዲያውቁት መደረጉን ገልጸው፣ ኮርፖሬሽኑ ያሉበትን ብዙ ተግዳሮቶች እንዲፈታ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ሰራተኛውና ማኔጅመንቱ ተደጋግፎ መስራቱ እንዲሁም ዋጋ ለማረጋጋት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል::
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከካይዘን ልህቀት ማዕከል ጋር የካይዘን ፕሮጀክት ትግበራ የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ሥነ-ሥርዓት መጋቢት 02/ 2016 ዓ.ም አካሄደ፡፡ የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱን አቶ አቻ ደምሴ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና አቶ ለቤዛ አለሙ የካይዘን ልህቀት ማዕከል የአገልግሎት ተቋማት ጥራትና ምርታማነት ማሻሻያ ዘርፍ ም/ ሥራ አስኪያጅ ተፈራርመዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ ከመጋቢት 5/ 2016 ዓ.ም እስከ ነሀሴ 30/ 2016 ዓ.ም ለሚተገበረው ችግር ተኮር ፕሮጀክት መር የአመራር ፍልስፍና የተመረጡ ቁልፍ የኮርፖሬሽኑ ችግሮችን በቀጣይነት ለመፍታት እና የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንዲሁም ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ አቶ አቻ ደምሴ ኮርፖሬሽኑ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች ለማስቀጠልና ውጤታማ ለመሆን ካይዘን ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑን ጠቅሰው ከካይዘን ልህቀት ማዕከል የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
አቶ ለቤዛ አለሙ በበኩላቸው የተሻሉ የካይዘን አማካሪዎችን በመመደብና የጋራ እቅድ በማውጣት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጠቁመው የኮርፖሬሽኑ አመራር ለካይዘን ትግበራ ለሚያደርገው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በሀገራችን ከህዳር 16 እስከ ታህሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም የተከበሩት ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን እና የፀረ ጾታዊ ጥቃት (የነጭ ሪባን) ቀንን በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ታህሳስ 20/ 2016 ዓ.ም አከበረ፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የኮርፖሬት የሕግ፣ ማህበራዊ ጉዳዮችና አሠራር ማሻሻያ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ አለም አቀፍ የኤድስ ቀን እና የፀረ ጾታዊ ጥቃት (የነጭ ሪቫን) ቀን በየዓመቱ የምናከብረው ለበአልነት ብቻ ሳይሆን ግንዛቤ ለመፍጠር በማሰብ ነው በማለት ሴቶችን ከማንኛውም ጥቃት መከላከል እንደሚገባ እንዲሁም ችላ እየተባለ የመጣው የኤችአይቪ ቫይረስ (ኤድስ) ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው በመጥቀስ የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ጤናቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በኮርፖሬሽኑ ሲካሄድ የቆየው ስፖርታዊ ውድድር ለአንድ ዓላማና ለአንድ ግብ በጋራ የመስራት የኮርፖሬት መንፈስን ለመፍጠር እንደተዘጋጀ ጠቁመው አንድ ጠንካራ የእግር ኳስ ቡድን በመመስረት በቀጣይ ከሌሎች ተቋማት ጋር ውድድር እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ስር በሚገኙት ንግድ ሥራ ዘርፎችና ዋናው መ/ቤት መካከል ለወራት ሲደረግ የነበረው የእግር ኳስ ውድድር ሲጠናቀቅ የፍጆታ እቃዎች ን/ሥ/ ዘርፍ (አለ በጅምላ) እግር ኳስ ቡድን የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡ በፍጻሜ ጨዋታ የፍጆታ እቃዎች ን/ሥ/ ዘርፍ የእህልና ቡና ን/ሥ/ ዘርፍን 4 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ዋንጫውንም ከኮርፖሬት የሕግ፣ ማህበራዊ ጉዳዮችና አሠራር ማሻሻያ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ እጅ በመቀበል ከደጋፊዎቻቸው ጋር በልዩ ህብረ ዝማሬ በመታገዝ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ በውድድሩ ሁለተኛ በመውጣት ጥሩ ተፎፎካሪ ለነበረው የእህልና ቡናን/ሥ/ ዘርፍ የእግር ኳስ ቡድን የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡
ከእግር ኳስ ውድድሩ ጎን ለጎን በሴት ሰራተኞች መካከል የሩጫ ውድድር የተካሄደ ሲሆን የማታወርቅ ንጉሴ ከዋና መ/ቤት በአንደኝነት ውድድሩን ያጠናቀቀች ሲሆን ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ ተወዳዳሪዎችና ለአንድ ልዩ ተወዳዳሪ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡