የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 916/2008 አንቀጽ 5 እና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 25/1984 አንቀጽ 47(1) መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 369/2008 ታኅሳስ 12 ቀን 2008 ዓ/ም በ3,836,000,000 (ሶስት ቢሊየን ስምንት መቶ ሰላሳ ስድስት ሚሊዮን ብር) የተቋቋመ የፌዴራል መንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡ በምስረታው የኮርፖሬሽኑ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ ሲሆን ከ2014 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የሚተዳደረው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር ነው፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ በተቋቋመበት ደንብ መሠረት በንግድ ዘርፉ በተናጠል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የኢትዮጵያ የእህል ንግድ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት (አለ በጅምላ)፣ የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ አክስዮን ማህበር (ኢትፍሩት) እና የግዥ አገልግሎት ድርጅት በኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ስር በንግድ ሥራና አገልግሎት ዘርፍነት ተዋቅረው የድርጅቶቹ መብቶችና ግዴታዎች ወደ ኮርፖሬሽኑ ተሸጋግሯል፡፡

 

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለማቋቋም ያስፈለገበት ዋና ምክንያት በንግዱ ዘርፍ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በተመሠረተ መደጋገፍና መተባበር በመሥራት የንግድ ግብይት ሥርዓቱን የተረጋጋ፣ ዘመናዊ፣ አስተማማኝና ውጤታማ ለማድረግ እንዲሁም በንግድ ሥራ ዘርፉ ተወዳዳሪ ተቋም ሆኖ ለመገኘት ነው፡፡

 

የኮርፖሬሽኑ የግብይት ማዕከላት

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የእህልና ቡና፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የፍጆታ ሸቀጦች ንግድ ሥራን በአዲስ አበባና በመላው የአገሪቱ ክልሎች ባሉ በ92 የእህል ግብይት ማዕከላት፣ 18 የአትክልትና ፍራፍሬ ማከፋፈያዎች እና 105 የችርቻሮ መሸጫ መደብሮች እንዲሁም የፍጆታ ዕቃዎች ሽያጭን በአዲስ አበባ (በመገናኛ፣ በቃሊቲ እና በመርካቶ) ባሉ 3 የሽያጭ መደብሮችና በክልሎች (በባህር ዳር፣ በደሴ፣ በሀዋሳና በሻሸመኔ) ባሉ 4 የሽያጭ መደብሮች የገበያ ማረጋጋት ሥራንና የግዢና ማማከር አገልግሎትን በማቀናጀት አገር አቀፍ አገልግሎት ይሰጣል