Consumer products 2

 

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በፍጆታ ሸቀጦች ንግድ መስክ በአገሪቱ የንግድ ሥርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ የተዛቡ የንግድ አሠራሮችን ለማስተካከል፣ ለዋጋ ግሽበት መንስዔ የሆኑ አሠራሮችን ለመፍታት፣ የተለያዩና በርካታ ሸቀጦችን በአንድ ሥፍራ ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ዘመናዊ የንግድ አሠራርን ለማስፈን እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ቀደም ሲል “አለ በጅምላ” መጠሪያ ይታወቅ የነበረው የንግድ ዘርፍ ሲመሠረት የተፈጠሩና የፋይናንስ ማነቆዎችንና ውጣ ውረዶቸን በመቋቋም ተልዕኮዎቹን በተለይም የገበያ ላይ ውድድርን በብቃት አሸንፎ ገበያን ከማረጋጋትና የህብረተሰቡን የመሠረታዊ ሸቀጦቸ ፍላጎት ከማሟላት እንዲሁም ለአገር ውስጥ አምራቾች የገበያ ዕድልን ከመፍጠር አኳያ እየሠራ ይገኛል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ በዚህ ዘርፍ ስላከናወናቸው ዓበይት ተግባራትና አገራዊ እንዲሁም በዓለመ አቀፍ ደረጃ በሁሉም ማኅበረ-ኤኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ የሚገኘው የኮቪድ-19 በሽታ በግብይት ሥራ ላይ ስላስከተለው ተጽዕኖ፣ አንዲሁም በሸማቹ ኅብረተሰብ በተለይም ዝቅተኛ የኤኮኖሚ አቅም ያላቸው ላይ የተፈጠረውንና ለወደፊትም ሊፈጠር የሚችለውን የሚፈጠረውን ኤኮኖሚያዊ ጫና ከመቋቋም አኳያ ዘርፉ በምርት ክምችትና እና አቅርቦት ረገድ እያከናወ ያለውን ሥራ በዚህ ጽሑፍ እንዳስሳለን፡፡

 

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አንድ የንግድ ዘርፍ የሆነው የፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ሥራ ዘርፍ በአለ በጅምላ ሥያሜ ሲቋቋም ምርቶችን 60 በመቶ ከውጭ በማስገባትና እና 40 በመቶውን ከአገር ውስጥ አምራቾች በመግዛት ነበር የአገሪቱን ገበያ የማረጋጋት ሥራን ሲከናውን ቆቷል፡፡ ዘርፉ በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ለማበርታትና የውጭ ምንዛሬንም ለማዳን ከውጭ የሚያስገባውን ምርት መጠን በመቀነስ አብዛኛውን ምርት ከአገር ውስጥ በመግዛት ለገበያ ያቀርባል፡፡ በዚህም ከበርካታ ኩባንያዎች ጋር የገበያ ትስስርን መፈጠር ችሏል፡፡ የንግድ ዘርፉ ለሽያጭ የሚያቀርባቸው ምርቶች (ለስላሳ መጠጦች፣ የፍጆታ ሸቀጦች ፣ የታሸጉ ምግቦች፣ የቤትና የግል ንጽሕና መጠበቂያዎች፣ የጽሕፈት መሣሪያዎች፣ የምግብ ዘይትና ስኳር ምርቶችን በመንግሥት በሚወጣ የዋጋ ተመን መሠረት እንደ መሣሪያ በመሆን ለኅብረተሰቡ ያደርሳል፡፡ የምርቶችን ሚዛናዊ ሥርጭት ለመረጋገጥም አካባቢው የሚገኙ የንግድ ቢሮዎች በሚያቀርቡት መረጃ መሠረት ምርቶችን በማሠራጨት የገበያ ማረጋጋት ሥራውን በከፍተኛ ደረጃ እያከናወነ ይገኛል፡፡

 

የንግድ ዘርፉ ለሸማቹ የሚያቀርባቸው አብዛኞቹ የለስላሳ መጠጦች፣ ዱቄት፣ የታሸጉ ምግቦች፣ የንጽሕና መጠበቂያዎች፣ መቆያና ጣፋጭ ምግቦች ሙሉ በሙሉ ለማለት ለሚያስችል ደረጃ ከአገር ውስጥ አምራቾች የሚቀርቡ ናቸው፡፡

 

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውና ተጽዐኖወ ከቀን ወደ ቀን እያየለ የመጣው የኮቪድ-19 በሽታ እንደማንኘውም የኤኮኖሚ ዘርፍና የንግድ ተቋም ሁሉ በኮርፖሬሽኑ የፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ላይ ተጽዐኖ ማድረሱ አልቀረም፡፡ ከዘርፉ እንቅስቃሴ ጋር በተየያዘ በሽታው የሠራተኞችን ሙሉ አቅም ተጠቅሞ ሥራዎቹም ማከናወን የሚችልበትን አቅም መቀነሱና በተወሰነ ደራጃመ ቢሆን ስን-ልቦናዊ ጫና ማድረሱ አልቀረም፡፡ በተለይም የዘርፉ የንግድ ሥራ ከውጭ ምርቶችን በዋነኝነት የበሽታው ሥርጭት በተስፋፋበት በጅቡቲ በኩል የሚገቡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአሽከርካሪዎችና በሌሎችም ላይ ስጋት ወለድ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ ለእነዚህ ችግሮቸ ሳይበገር የተወሰኑ ሠራተኞች በፈረቃና ከቤት ሆነው መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት በዚህ ወቅት እንደ ወታደር ከፊት በመቆም ኅበረተሰቡ የምግብና ሌሎች የፍጆታ ዕቃዎችን ማግኘት እንዲችልና የተቸገሩ ሰዎችም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተለይ በዱቄት፣ በፓልም ዘይት፣ በፓስታና ማካሮኒ አቅርቦት ረገድ ከወትሮው በተለየ የላቀ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

 

በበሽታው ምክንያት የኤኮኖሚ ተጽዕኖ ስር ለወደቁ ወገኖች በተለይም ለአረጋውያን ዕርዳታ የሚያደርጉ ድርጅቶች ከክፍለ ከተማ እና ከከተማ አስተዳደሩ ይዘው በሚመጡት መረጃ መሠረት የዱቄት፣ ፓስታ፣ ማካሮኒና ሌሎችንም ምርቶች ያለምንም ውጣ ውረድ ገዝተው እንዲያቀርቡ አስተዋጽዖ እያደረገ ይገኛል፡፡

 

የበሽታው የሥርጭት አድማስ እየሰፋ ከመሄድ አኳያ ወደፊት ሊፈጠር የሚችለውን የሸቀጥ እጥረት ከወዲሁ ለመከለከልም በተጨማሪም የንግድ ዘርፉ የሽያጭ ማዕካት በሚገኙባቸው በሁሉም አካባቢዎች ለሚገኙ አስከ 97 ሺህ የሚደርሱ የመንገሥት ሠራተኞች በወርኃዊነት የቀጥታ ግዢ እንዲፈጽሙ በማድረግ ተጽዕኖውን ለመቀነስ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ ለአብነትም ከ46 ኮንቴይነር በላይ ፈሳሽ ዘይት ከውጭ በማሰመጣት እንዲሁም በቂ የዱቄት ምርት በመያዝ በሁሉም የሽያጭ መጋዘኖች በበቂ ሁናቴ እንዲኖር በማድረግ ሊከሰት የሚችለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የተቻለ ሲሆን ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ተጠቃሚዎች የሽያጭ አገልግሎት እንዲያገኑ ተደርጓል፡፡

 

ለኮርፖሬሽኑ የሚቀርብ ምርትን በተመለከተ በተለይ ከውጭ የምርት ግብዓቶችን (ጥሬ ዕቃ) አስመጥተው የሚያመርቱ ኩባንያዎች ላይ ኮቪድ-19 ችግር መፍጠሩ አልቀረም፡፡ በዚህ ረገድ ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ አማራጮችን በመውሰድ ምርት በቅድሚያ የሚያገኝበትን ዕድል በመፍጠር ከምንጊዜውም በተሻለ ሁኔታ ምርት በመጋዘን በመያዝ ለማኅበረተሰቡ ምርቶችን ተደራሽ በማድረስ ላይ ነው፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ፣ በደሴና በሻሸመኔ ቅርንጫፎች በቂ ምርት እንዲኖር ተደርጓል፡፡

 

ሠላም ለሁሉም ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መሠረት ነው፡፡ ሠላም በታጣ ቁጥር አምራችና የንግድ ተቋማት ሁሌም ስጋት ውስጥ መውደቃቸው አይቀርም፡፡ በቅርቡ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በአገሪቱ በተከሰተው ሁከት ምክንያት በአዲስ አበባና ሻሸመኔ የሚገኙ የኮርፖሬሽኑ የፍጆታ ዕቃ መደብርና መጋዘኖች በመዘጋታቸው ለተወሰኑ ቀናት ለኅብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ሳይቻል ቀርቷል፡፡ በሌላም በኩል የተስተጓገለውን የሽያጭ አገልግሎት የደሴ፣ የባህር ዳርና የአዋሳ የሽያጭ መደብሮች ተጨማሪ አቅም ፈጥረው እንዲሠሩ በማድረግ ለማካካስና ችግሩን ለመቋቋም ጥረት ተደርጓል፡፡

 

ኢንሥኮ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የንግድ ሥራውን አፈጻጸምና ፋይዳ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ዕቅድ ነድፎ መንቀሳቀስ ከጀመረ ሰነበብቷል፡፡ በተለይም ለኦፕሬሽን ሥራዎች ልቀት ቀዳሚ ትኩረት በመስጠት በግዥና ሽያጩ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ለአምራቹ ገበያ የመፍጠር ዕድል እና የሸማች ገበያን የማረጋጋት ሚና በአግባቡ ለመወጣት እየሠራ ይገኛል፡፡ በፍጆታ ሸቀጦች ግብይት እንቅስቃሴ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች አንዱ የሽያጭ መደብሮችን ቁጥር ከፍ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ከክልሎች ጋር ተቢውን ተግባቦት በማካሄድ በየዓመቱ ቢያንስ ሁለት ተጨማሪ የሽያጭ መጋዘንና መደብሮችን በመክፈት ለህብረተሰቡ በተሻለ ተደራሽ ለመሆን ታስቧል፡፡ በጅማ፣ አዳማ፣ መቀሌ፣ ጎንደርና ወልቂጤ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውም ታውቋል፡፡

 

የአገር ውስጥ አምራቾች ጋር በተሻለ ቅርበት በመሥራትና የአገር ውስጥ ምርትን በማበረታታት የኅብረተሰቡን ፍላጎት ያገናዘበ አግልገሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ተገባራት ም የስትራቴጂክ ዕወቅዱ አካላት ናቸው፡፡ ይህም ተጨማሪ የሥራ ዕድልን፣ አገልግሎትንና ትርፍን የሚያስገኝ በመሆኑ የኮርፖሬሽኑን አቅም የማጠናከር አቅም እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

 

ከውጭና ከአገር ውስጥ አምራቾ ጋር የተጠናከረ ግንኙነት በማረግ በቂና አስተማማኝ የምርት አቅርቦት እንዲኖር የማድረግ፣ እንደ ዲመሬጅ ያሉ አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስ እንዲሁም መጠነ ሰፊ ማዕካለዊ መጋዘን በማስገንባት በቂ ስቶክ ለመያዝና በጥቅሉ የገበያ ላይ ተወዳዳሪነትንና ትርፋማነትን ለማሳደግ ተወጥኗል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ በዚህ የንግድ ዘርፍ ቶሎ ቶሉ በሚሸጡ የፍጆታ ሸቀጦችን ግብይት ላይ የተሠማራ ከመሆኑ አኳያ ሁሉንም የኮርፖሬሽን ዘርፎች ይዞ መውጣት የሚችልበት እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ለዚህ ማነቆ የሆኑ በተለይም ከሂሳብ መዝጋትና ተገቢ ያልሆኑ ዕዳዎችን ከማሠረዝ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረቶች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከስትራቴጂያዊ ሥራዎች በተጓዳኝም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ  ለመደበኛ ሥራዎች ሰፊ ትኩረት በመስጠትና በጠነከረ አቅም በመሥራት ወደ ትርፋማነት ለመምጣት እየተሠራ የሚገኝ ሲሆን፤ የኮርፖሬሽኑ አዲስ አመራር ከዕዳ ክፍያ ጋር ለተያያዙ ማነቆዎች እልባትን በማስገኘት ጠንካራና ለሌሎች ተጓዳኝ የኮርፖሬሽኑ ሥራዎች ጭምር አቅምን ሊፈጠሩ የሚችሉ ሥራዎችን ለመከወን እየሠራ ይገኛል፡፡