የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2013 ዕቅድ አፈጻጸምና በ2013 የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ከሁሉም የንግድ ዘርፎችና ከኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት ሠራተኞች ጋር አጠቃላይ ውይይቶች አካሂዷል፡፡ ውይይቶቹ በኢንሥኮ የበላይ አመራሮች ሰብሳቢነት የተካሄደ ሲሆን የተሳታፊዎቸን ለኮቪድ-19 ተጋላጭነት ለመቀነስ በሚያስችል መልኩ በዙር ጎተራ በሚገኘው ኮርፖሬሽኑ የስብሰባ አዳራሽ ነሀሴ 21፣ 22፣ 25፣ 26 እና 28 ቀን 2012 ዓ/ም ተካሂደዋል፡፡

የኢንሥኮን የ2012 ዓ/ም የንግድ ሥራዎች የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት ላይ ሽፋን ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የተቋሙ የ2012 ዓ/ም የግዢና አፈፃፀም የሽያጭ አፈፃፀም፣ ገበያን ከማረጋጋት አንፃር የተከናወኑ ዓበይት ተግባራት የሚገኙበት ሲሆን የሰው ሀብት ሥራ አመራርና ልማት፣ የፋይናንስ ሀብት አጠቃቀም፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽን፣ የሪፎርምና የመልካም አስተዳደርና ሌሎችም ተቋማዊ ዕቅዶች አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የግዢ ዕቅድ አፈጻጸምን በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ 10.3 ሚሊዮን ኩንታል እህል፣ ቡና፣ የፍጆታ ዕቃዎች እና አትክልትና ፍራፍሬ በብር 11.3 ቢሊዮን ለመግዛት አቅዶ 7.9 ሚሊዮን ኩንታል በብር 8.7 ቢሊዮን በመግዛት የዕቅዱን በመጠንም ሆነ በዋጋ 77 በመቶ ማከናወኑ ተገልጿል፡፡

የሽያጭ አፈፃፀምን በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ በ2012 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥና በውጪ ገበያ ብር 8.9 ቢሊዮን ዋጋ ያለው 10.1 ሚሊዮን ኩንታል እህል፣ ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የፍጆታ ዕቃዎች እንዲሁም የግዢና ማማከር አገልግሎት ለመሸጥ አቅዶ ብር 5.9 ቢሊዮን ዋጋ ያለው 7.0 ሚሊዮን ኩንታል ምርትና አገልግሎት በመሸጥ ዕቅዱን በመጠን 70 በመቶ በዋጋ ደግሞ 67 በመቶ ማከናወኑ ተጠቅሷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ሲሚንቶ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያሰራጭ በመንግሥት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከፋብሪካዎች በመረከብ በሥርጭት እንዲሸፍናቸው በተሰጡት አካባቢዎች የ25.8 ብር ሚሊዮን ዋጋ ያለው 83.6 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ ጠቅላላ ሽያጭ አከናውኗል፡፡

በግዢና ሽያጭ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ ካሳደሩ ምክንያቶች መካከል የመግዣ ካፒታል እጥረት፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ምርትን የማስተዋወቅና ገበያ የማፈላለግ ሥራ በበቂ ሁኔታ አለመሠራቱ፣ እሴት ጨምሮ መሸጥ ላይ ትኩረት አለመደረጉ፤ የውጭ ደንበኞች የሚሠጡት ዋጋ በተለይም የቡና፣ ቅባት እህልና ጥራጥሬ ዋጋ ወጪን ሸፍኖ ለመሸጥ የማያስችል ዝቅተኛ ዋጋ መሆን፤ የግል ላኪዎች በኤክስፖርት የሚደርስባቸው ኪሣራ በሚያስገቡት ሸቀጥ ስለሚያካክሱት ዋጋ ሰብረው መሸጣቸውና በሚፈለገው መጠን ለሽያጭ መደብሮች የሸቀጥ አቅርቦት ማቅረብ አለመቻሉ፤ ከባንክ ኦቨር ድራፍት /ብድር/ በመግባት እንዲፈታ እየተደረገ ቢሆንም ብድሩ ከፍተኛ የወለድ ወጭ ያለው መሆኑ፣ የሀገር ውስጥ ስንዴ መግዣ ዋጋ በእጅጉ መጨመር፤ በኮሮና ፋይረስ ወረርሽን ምክንያት የእህል አቅርቦት መቀነስና የዋጋ መጨመር፤ የሚሉት ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች ይገኙበታል፡፡

የአመራሩን ሁኔታ በተመለከተም አመራሩ የተሰጠውን ተግባር በቅንነት ተቀብሎ ለመፈፀም ጥረት የሚያደርግ መሆኑ፤ የነበረውን የአመራር ክፍተት ሸፍኖ በመስራት በኩል የነበረው እንቅስቃሴ በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ የነበሩትን ችግሮች ለይቶ የተሸሻሉ አሰራሮቸን ሥራ ላይ በማዋል የተቀናጀ እንቅስቃሴ መደረጉ አንዲሁም ኮርፖሬሽኑን ትርፋማና ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት አበረታች መሆኑ በጥንካሬ የተመላከተ ሲሆን በየዘርፉ የተበተነ አሠራር መኖሩ፤ ተቋሙ እንደ ኮርፖሬሽን የተደራጀና የተጠቃለለ ሆኖ አለመመራቱ፤ ከቀመጡ የአሠራር መመሪያዎች ውጭ የሚፈፀሙ ተግባሮች መኖራቸው በድክመትነት ተገምግመዋል፡፡

በቀጣይ እንደ ተቋም አፈጻጸምን ለማሳደግ በትኩረት አቅጣጫነት ከተቀመጡ ጉዳዮች መካከልም አፈጻጸሞች አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ጉድለትና ድክመት የታየባቸውን በማሻሻል ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር አልሞ መስራት፣ ውጤታማ የሀብትና ንብረት አጠቃቀምን ተግባራዊ ማድረግ፣ የተለያዩ የገበያ መረጃዎችን በጥራትና በስፋት ከአምራቹ፣ ከአቅራቢው፣ ከተጠቃሚው በማሰባበስብ ሥራ ላይ ማዋል፤ በወጪ ንግድ ያላሰለሰ ጥረትና ድጋፍ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሣደግ እንዲሁም ልዩ ልዩ አጋዥ ሪፎርሞችን ሥራ ላይ ማዋልና የደንበኞችንና ባለድርሻ አካላትና ተጠቃሚዎችን እርካታ ማሣደግ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የጋራ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡