የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሚያካሂዳቸውን የንግድ ሥራዎች በተሻሻሉ የአሠራር ዘዴዎች በመደገፍና ዘመናዊ፣ ወጪ ቆጣቢና የተቀላጠፈ አሠራርን ሥራ ላይ ለማዋል የሚረዱ የተለያዩ ዕቅዶችንና የአሠራር ስልቶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል ቀደም ሲል በመመሪያ ላልተደገፉ የተለያዩ የተቋሙ አሠራሮች መመሪያዎችን በማዘጋጀትና የነበሩትንም በማሻሻል የአገልግሎት አሠጣጥንና የስትራቴጂያዊ ግቦችን ስኬታማነት ማረጋገጥ ይገኙበታል፡፡ በዚህም ረገድ በተዘጋጁ ረቂቅ መመሪያዎች ዙሪያ የኮርፖሬሽኑን የበላይ አመራርና የሥራ ኃላፊዎች ያሣተፈ ውይይት ነሀሴ 12 ቀን 2013 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ውይይት ከተካሄደባቸው ረቂቅ መመሪዎች መካከል የዕውቅናና ሽልማት አሰጣጥ፣ የተሸከርካሪ ስምሪት እንዲሁም የሥልጠናና ትምህርት መመሪያዎች የሚገኙበት ሲሆን ከተሣታፊዎች ጋር በተካሄዱ ውይይቶች የተገኙ ግብዓቶችን በመቀመር በቅርቡ ጸድቀው በኮርፖሬሽን ደረጃ ተግባራዊ እንደሚደረጉ በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡