001_6.jpg

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አመራርና ሠራተኞች በአራተኛውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር “የገበያ ማረጋጊያ ሥራችንን እያጠናከርን አረንጓዴ አሻራችንን እናሣርፋለን” በሚል መሪ ቃል ሆለታ በሚገኘው የኮርፖሬሽኑ የግብይት ማዕከል የችግኝ ተከላ አካሂደዋል፡፡ ከተለያዩ የኮርፖሬሽኑ የንግድ ሥራ ዘርፎች የተውጣጡ ሠራተኞችና የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ቅዳሜ ሀምሌ 23 ቀን 2014 ዓ/ም በተካሄደው መርኃ ግብር ላይ ከ1,300 በላይ የቅመማ ቅመም፣ የፍራፍሬ፣ የግቢ ውበትና የጥላ ዛፎች ተከላ የተካሄደ ሲሆን በተመሳሳይ መርኃ ግብሮችም በኮርፖሬሽኑ የተለያዩ ቅርንጫፍ ማዕከላት መሰል የተከላ መርሃ ግብሮች ተከናውነዋል፡፡

 

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ በችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ኮርፖሬሽኑ በተለይም ካለፉት አራት በተካሄዱት አረንጓዴ ዐሻራ የማኖር አገራዊ ጥሪዎች የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ክንውኖችን በስፋትና በተከታታይነት ሲያካሂድ መቆቱን አስታውሰው፤ እስካሁን በተካሄዱ የተከላ መርኃ ግብሮች ከተተሉት ችግኞች 84 በመቶው መጽደቃቸውን ገልጸዋል፡፡ በያዝነው ዓመትም ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ የቅመማ ቅመም፣ የፍራፍሬ፣ የውበትና የጥላ ዛፎችን በሆለታ የግብይት ማዕከልና በሌሎችም የኮርፖሬሽኑ ቅርጫፍ ማዕከላት በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

 

የችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ የደን ሽፋንን ለማሳደግ ብሎም አረንጓዴ ልማትን ለማረጋገጥ ከሚኖረው አስተዋጽዖ በተጨማሪ መልሰው ምርት መስጠት የሚችሉ ችግኞች የሚለሙበት በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

የአረንጓዴ ልማት እንዲሳካ እንደ አገር ሰፊ ርብርብር እየተደረገ መሆኑን ያወሱት ዋና ሰራ አስፈጻሚው፤ በተለይም ዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት እየተስተዋሉ የሚገኙ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና አፈር ለምነት እጦትን ለመከላከል የችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ከመሆኑ አኳያ ሁሉም በየአካባቢው ሥራውን በተገቢው መልኩ ለመከወን የሚያስችል በቂ ዝግጅት፣ ትግበራና ክትትል በማድረግ የበኩሉን የልማት አስተዋጽዖ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡