Evaluation.jpg

 

የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የበጀት ዓመቱ እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ከነሐሴ 2-4/ 2014 ዓ.ም የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የዘርፎች ሥ/ አስፈጻሚዎችና እስከ ቡድን መሪ ያሉ የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ ለሶስት ቀናት የተካሄደው መድረክ ዓላማ፣ በበጀት ዓመቱ ታቅደው የነበሩ ስራዎች ክንውን በመገምገም የነበሩ ጥንካሬዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የታዩ ችግሮችን ከምንጩ ለይቶ መፍትሄ በማስቀመጥ በ2015 በጀት ዓመት ውጤታማ ስራ ለመስራት ነው፡፡

በውይይቱ ለህብረተሰቡ በገበያ ማረጋጊያነት የሚቀርቡ መሰረታዊ የምግብ እህል ምርቶች፣ የፍጆታ ሸቀጦች፣ አትክልትና ፍራፍሬ አቅርቦት፣ ስርጭትና ተደራሽነት እቅድ አፈፃፀሙ ከደንበኞች ፍላጎት አንጻር መሆኑን የፋይናንስ ስራው በሲስተም በሚፈለገው ደረጃ IFRS ሂሳብ የመዝጋት አመታዊ የፋይናንስ ሪፖርትን በተሰጠ ግዜ ገደብ የማውጣት ሂደት ተከትሎ መሰራቱን እንዲሁም የሰው ሃብት ለማብቃት እና ሀብት አጠቃቀምን አሳድጎ ያለ ስራ የተቀመጡ ንብረቶችን አንቀሳቅሶ ውጤታማ ለማድረግ የተሰሩ ሥራዎች አፈፃፀም ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ ግምገማውን ሲያጠቃልሉ በአጠቃላይ በኮርፖሬሽን ደረጃ በዘርፎች፣ በዳይሬክቶሬቶች እና ጽ/ቤቶች በእቅድ አፈጻጸሞች ላይ የተደረገው ውይይት በባለቤትነት መንፈስ እና የኮርፖሬሽኑን ተልእኮ ለማሳካት እና ለህብረተሰቡ የምንሰጠውን አገልግሎት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በበጀት ዓመቱ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፣ ያልተሰሩ ስራዎች በድክመታችን አለመከናወናቸውን ተቀብለን ሁሉንም ችግር በአንዴ መፍታት ባይቻል ቅድሚያ ለሚሰጠው ጉዳይ ቅድሚያ እየሰጠን እንሰራለን ብለዋል ፡፡