photo_2022-11-04_15-15-58.jpg

 

ኮርፖሬሽኑ ከዋና መ/ቤት ጀምሮ በሁሉም ዘርፎችና የክልል ግብይት ማእከላት ለሚገኙ የሥራ ሃላፊዎች እና ሰራተኞች የ2014 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2015 በጀት ዓመት የእቅድ ትውውቅ የማጠቃለያ መድረክ በአዳማ ከተማ ከጥቅምት 19-20/ 2015 ዓ.ም አድርጓል፡፡ ከማጠቃለያ መድረኩ አስቀድሞ በአዲስ አበባ (በሁለት ዙር)፣ በአዳማ፣ በሃዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በደሴና በባህር ዳር ተመሳሳይ መድረኮች ተካሂደዋል፡፡

በማጠቃለያ መድረኩ ላይ የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚዎችና የዘርፎች ሥ/ አስፈጻሚዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ የጽ/ ቤት ኃላፊዎችና የአራቱ ንግድ ስራ ዘርፎች በየደረጃው ያሉ የሥራ ሃላፊዎች እስከ ከፍተኛ ባለሙያ ተገኝተዋል፡፡ የውይይቱ ዋና ዓላማ በበጀት ዓመቱ ታቅደው የነበሩ ስራዎችን ክንውን በመገምገም የነበሩ ጥንካሬዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የታዩ ችግሮችን ከምንጩ ለይቶ በ2015 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸምን አስመልክቶ በቀረበው ሪፖርት የመሠረታዊ ፍጆታ አቅርቦት /ግዥ/ የምርት ስርጭትና ተደራሽነት /ሽያጭ/ አፈፃፀም የአቅርቦት እጥረትንና የዋጋ ንረት ለመከላከል የተደረገ ጥረት በዝርዝር ቀርቦ አፈጻጸሙ ላይ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የ2015 በጀት ዓመት እቅድን አስመልክቶ እቅዱ ሲዘጋጅ በየዘርፉ የቀረበውን ፍላጐት አቅምን ያገናዘበና ተልዕኮን ለማሳካት ቅድሚያ ትኩረት የሚሠጣቸውን በመለየት የተሰራ መሆኑን፣ ያለፉት በጀት ዓመታት ዕቅድ አፈፃፀም እንደ መነሻ በታሳቢነት የተወሰዱ መሆናቸው እና ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ የሁኔታ ትንተናዎች ግምት ውስጥ መግባታቸው በቀረበው ገለጻ ተመላክቷል፡፡ እቅዱ በዋነኛነት የገበያ ማረጋጋት ሥራን እና የገበያ ድርሻን በማሳደግ ዋናውን የኮርፖሬሽኑን ተልዕኮ ለማሳካት የሚያስችል እንዲሆን ታስቦ መዘጋጀቱ በገለጻው ተጠቅሷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ እቅዱ ከያዛቸው ዋና ዋና ግቦች መካከል የግዢ ዕቅድን ስንመለከት በ2015 በጀት ዓመት ከተለያዩ የግዢ ምንጮች 3,102,318 ኩንታል ምርት በብር 11,104,108,556 ለመግዛት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን የሽያጭ ዕቅድን በተመለከተ ደግሞ ኮርፖሬሽኑ በ2015 በጀት ዓመት የማረጋጋቱን ሥራ ጨምሮ በአገር ውስጥ እና በወጪ ግብይት ብር 12,674,763,285 ዋጋ ያለው ምርትና አገልግሎት ለመሽጥ ዕቅድ ይዟል፡፡ ከዚህ ውስጥ የሀገር ውስጥ ሽያጭ 12,069,480,785 ብር እና ኤክስፖርት ሽያጭ 605,282,500 ብር ይይዛሉ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ በማጠቃለያ መድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በ2015 በጀት ዓመት እቅድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ሁሉንም አቅም በመጠቀም የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለው ከጠቀሷቸው ተግባራት መካከል የግዢ አፈጻጸም ትስስር፣ የደንበኞች አያያዝ፣ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንዲሁም የሥራ አፈጻጸም አሞላልና ነጥብ አሰጣጥ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ኦፕሬሽናል ልቀት፣ የመፈፀም እና ማስፈፀም አቅም፣ የማያቋርጥ ለውጥና ተወዳዳሪነት እንዲሁም ስትራቴጂያዊ አጋርነት የኮርፖሬሽኑ የትኩረት መስኮች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡