አዳዲስና ዘመናዊ አሰራር ለዘረጉ፣ የላቀና ተጨባጭ እድገት ላስመዘገቡ፣ መልካም ስማቸውን ጠብቀው ለአመታት በትጋት ለዘለቁ ተቋማት /MILESTONE, BRANDING AND REPUTATION/ አቢሲኒያ የጥራት ድርጅት እውቅና ለመስጠት ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ/ም በኢንተርሊግዠሪ ሆቴል (በቀድሞ ኢንተርኮንቲኔታል ሆቴል) ባዘጋጀው የኢንደስትሪ ሽልማት መርሃ-ግብር ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ /ኢትፍሩት/ የከፍተኛ ክብር ሽልማት የወርቅ ዋንጫ፣ የወርቅ ሜዳሊያና የከፍተኛ ክብር ዲፕሎማ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

ለዘርፉ ስራ አርዓያ የሆኑ አምስት ምርጥ ሰራተኞች የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት ሲሸለሙ፣ የመካከለኛ ደረጃ ሁለት አመራሮች ደግሞ የኒሻን ተሸላሚ ሆነዋል፤ እንዲሁም የዘርፉ ስራ አስፈጻሚ የከፍተኛ ክብር (የኮርዶን) ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ይህ በሀገራችን በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተካሄደ የመጀመሪያው የሽልማት መርሀ ግብር ሲሆን ከ57ሺህ የኢንዱስትሪ ተቋማት የተመረጡት 50 ብቻ ሲሆኑ በአጠቃላይ ተቋማዊ ውጤታቸው ላይ ከ2009-2014 በተደረገ ውጫዊ ምዘና በ24 መሰረታዊ መለኪያዎች ላይ ተመስርቶ በተገኘ ውጤት እንዲመረጡና እንዲሸለሙ መደረጉን በሽልማት መርሃ -ግብሩ ወቅት ተገልጿል፡፡
በዚህ የሽልማት ፕሮግራም ላይ የኮርፖሬሽኑ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሃሰን መሃመድ፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ እና የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮችና ዳይሬክተሮች እንዲሁም በዘርፉ ጥሪ የተደረገላቸው የዘርፉ ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡

ዘርፉ ይህንን ከፍተኛ ሽልማት ያገኘው በኮርፖሬሽኑ የስራ አመራር ቦርድ እና የኮርፖሬሽኑ ማኔጅመንት በሚሰጠው ስትራቴጂካዊ አመራር በመመራት፣ የዘርፉ ማናጅመንትና ሠራተኞች ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች ባደረጉት እገዛና ድጋፍ በመሆኑ ሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ፤ ደስ አለን እያለ፣ ዘርፉ ይህንን ስኬት እንዲያስመዘግብ ድጋፍና እገዛ ላደረጉ የኮርፖሬሽኑ ቤተሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል፡፡

የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ስራ ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት ትኩስና ጥራታቸውን የጠበቁ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ይታወቃል፡፡