DSC_0995_032358.JPG

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከራስ ቴአትር ጋር በመተባበር የ2016 ዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ሆስፒታሎች ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማንና ወላጅ እናቶች በዓሉን ምክንያት በማድረግ ስጦታ የማበርከትና የመልካም አዲስ ዓመት ምኞት መግለጫዎችን የማስተላለፍ መርኃ ግብር አካሄደ፡፡

ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ/ም በተካሄደው በዚህ የእንኳን አደረሳችሁ ጉብኝትና የስጦታ መርኃ ግብር ኮርፖሬሽኑ በ160 ሺህ ብር ወጪ የተለያዩ የታሸጉ ምግቦች፣ ፍራፍሬና የንጽህና መጠበቂያዎች በማዘጋጀት በጥሩነሽ ቤጂንግ፣ በአበበች ጎበና፣ በምኒልክ፣ በዘውዲቱ፣ በራስ ደስታ፣ በየካቲት 12 እና በጋንዲ ሆስፒታሎች በመገኘት ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን፣ እናቶችና ህጻናት ከቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች ጋር በመሆን አበርክቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የማኅበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት ዓለማየሁ በመርኃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ኮርፖሬሽኑ እየተገበረ ከሚገኛቸው የአገር ውስጥ ገበያን የማረጋጋት፣ ለአምራቹ ገበያን የመፍጠርና የኤክስፖርት ግኝትን የማሳደግ ተልዕኮዎች በተጓዳኝ በተለያዩ የማኅበራዊ ኃላፊነት ትግበራ ላይ በመሣተፍ የህብረተሰብ አጋርነቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጎለበተ መምጣቱን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመትም ለየት ባለ መልኩ ከራስ ቴአትር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በተለይ በአዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች ሴቶችና ህጻናት ላይ በማተኮር ለ250 ህሙማን በሰው አምስት መቶ ብር የሚሆኑ የኮርፖሬሽኑን ምርቶች በመያዝ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የማስተላለፍ፣ ታማሚዎችን የማጽናናትና ድጋፍ የማድረግ ተግባር መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም ኮርፖሬሽኑ ይህን አቅመ ደካሞችን የመርዳት ተግባሩን እያጠናከረ እንደሚሄድ ቃል የገቡት ወ/ሮ ትዕግስት፤ በዚህ ረገድ መሰል ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ” የሚለውን የሀገራችንን ብሂል ወደ ተግባር በመለወጥ በተለይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚታዩባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመለየትና አቅሙ የፈቀደውን ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡