Management_News2.jpg

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ስራ አመራር የ2016 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸምን ገመገመ፡፡ በኮርፖሬሽኑ ስር የሚገኙ ዘርፎች፣ የዋና መ/ቤትና የኮርፖሬት ሎጀስቲክስና ቴክኒክ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የሩብ ዓመት እቅድ ክንውን በዝርዝር ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በሩብ ዓመቱ በአጠቃላይ ሊገዛው ያቀደው መሠረታዊ የምርት አቅርቦት መጠን ብር 1,442,305,115 ዋጋ ያለው 297,648 ኩንታል ሲሆን በዚህ ወቅት ብር 2,778,723,940 ዋጋ ያለው 498,031 ኩንታል በመግዛት የዕቅዱን በመጠን 167 በመቶ፤ በዋጋ ደግሞ 193 በመቶ ማከናወኑ በቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ተመልክቷል፡፡

ሽያጭን በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ በሩብ ዓመቱ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ገበያ ብር 2,920,244,100 ዋጋ ያለው 543,820 ኩንታል መሠረታዊ ምርትና አገልግሎት ለማሰራጨት አቅዶ ብር 2,665,653,200 ዋጋ ያለው 483,427 ኩንታል ምርትና አገልግሎት በማሰራጨት ዕቅዱን በመጠን 89 በመቶ በዋጋ ደግሞ 91 በመቶ አከናውኗል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ የእቅድ አፈጻጸም ግምገማውን በመሩበት ወቅት በሩብ ዓመቱ በትንሽ ጥረት የታየው አፈጻጸም አበረታች እንደሆነ ገልጸው በቀሪዎቹ ዘጠኝ ወራት የበለጠ በመስራት የላቀ ውጤት ማምጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቀጣይ ዋና የትኩረት አቅጣጫ መሆን አለባቸው በማለት በዝርዝር ካቀረቧቸው ጉዳዮች መካከል ግዢና ሽያጭን ሁልግዜ በሁሉም መደብር/ቅርንጫፍ መተግበር፣ ገቢን ማሳደግ፣ እያንዳንዱን ፈጻሚ በውጤት መመዘን፣ ወጪ ቆጣቢ ስልት መጠቀም፣ ነባሩን በማጠናከር አዳዲስ የምርት አቅርቦት ላይ መስራት፣ የፋይናንስ ሥራን ማጠናቀቅ (IFRS/ኦዲት)፣ ትልቅ ገቢ የሚያመጡ ስራዎች ላይ ማተኮር የሚሉት ይገኙበታል፡፡