በአዲስ አበባ ከተማ ህዳር 11/ 2016 ዓ.ም በተካሄደው የኮርፖሬሽኑ የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ክንውንና የ2016 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ ማጠቃለያ ላይ የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ አብዲ ሙመድ በተገኙበት በቦርዱ ውስጥ የተጓደለን የሰራተኛ ተወካይ ለመተካት ምርጫ ተካሄደ፡፡

ምርጫውን ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት ከዚህ ቀደም የሰራተኛ ተወካይ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ አማረ ዳምጤ እና አቶ ሳለጌታ በላይ መልቀቂያ በማስገባታቸው እንደሆነ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ ገልጸዋል፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚው አያይዘውም ከዚህ ቀደም በቦርዱ ውስጥ ሁለት የሰራተኛ ተወካዮች የነበሩ ሲሆን የሚወከለው ሰራተኛ አንድ እንዲሆን በመወሰኑ ምክንያት ከዚህ ቀደም ተወካይ የነበሩት ሁለት ግለሰቦች ለሰራተኛው ክብር ሲሉ ጠቅላላ ጉባኤው የሚወክለውን ሰራተኛ እስኪመረጥ ራሳቸውን ከቦርድ አባልነት ማግለላቸውን አብራርተዋል፡፡

የምርጫ ሂደቱን የመሩት አቶ አብዲ ሙመድ በሰራተኛው የሚወክለው ግለሰብ የሰራተኛውን ጥቅም የሚያስከብር፣ የተቋሙን ተልእኮ የሚያሳካ፣ ተቋሙ የበለጠ እንዲያድግና ትርፋማ ሆኖ እንዲቀጥል የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት፣ አርአያ የሚሆንና ብቃት ያለው መሆን እንዳለበት ገልጸው የሚወከለው ሰራተኛ በሚፈለግበት ጊዜ በቀላሉ እንዲገኝ ከአዲስ አበባ እንዲሆን አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሰረት የእጩዎች ምርጫና የድምጽ መስጠት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

የዕጩዎችን ብዛት በተመለከተ በተሰጠ ድምጽ 3፣ 5 እና 6 የሚሉ አማራጮች ቀርበው 5 የሚለው በአብላጫ ድምጽ የተወሰነ ሲሆን ከቀረቡት እጩዎች መካከል ወ/ሮ ኤልሳቤት ታደሰ በ274 አብላጫ ድምጽ ተመርጠዋል፡፡ አቶ አበዋ ጌትነት በ142 ድምጽ በተጠባባቂነት ተመርጠዋል፡፡

10.jpg

በአብላጫ ድምጽ የተመረጡት ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ታደሰ