በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽንን ያለፉት ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ጥር 8/ 2016 ዓ.ም በአካል ተገኝተው ግምገማ አካሄዱ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዱ የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የፍጆታ ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት አበረታች ስራዎችን ስለመሰራቱ ጠቁመው፤ ነገር ግን የአፈጻጸም ጉድለት ያለባቸውን በስፋት አቅዶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል::

የኢትዮጰያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቻ ደምሴ የቋሚ ኮሚቴው አባላትን በአከል ተገኝተው ግምገማ በማድረጋቸው አመስግነው፤ በኮሚቴው እየተደረገ ያለው ድጋፍ ጥሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር እና ህገ ወጥ የንግድ ስርአት ለተቋሙ ተግዳሮት እንደሆነ ተናግረው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙት የተቋሙ ይዞታዎች ከህግ አግባብ ውጪ እየተወረሰ በመሆኑ የተቋሙ ህልውና አደጋ ላይ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚው አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑ ባለፉት 6 ወራት ካቀረባቸው የሽያጭ ምርቶች ከመደበኛው የግብይት ዋጋ በጠቅላላው 1.3 ቢሊዮን ብር ተቀናሽ በማድረግ በገበያ ማረጋጋቱ ስራ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከቱን በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የኮርፖሬሽኑን ያለፉት ስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸምን ከመገምገም ባለፈ ከኮርፖሬሽኑ መሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም ቃሊቲ የሚገኙትን የፍጆታ እቃዎች ንግድ ስራ ዘርፍ መደብርና የቡና ማእከል፣ ሳሪስ የሚገኘውን የእህል ማከማቻና ማደራጃ ማእከል እንዲሁም የኮርፖሬት ሎጀስቲክስና ቴክኒክ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የስራ እንቅስቃሴ ከጎበኙ በኋላ  ግብረ መልስ ሰጥተዋል::

በማጠቃለያው የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዱ ከኮርፖሬሽኑ ተልእኮ ጀምሮ ግልጽነት ስለመፈጠሩና ተቋሙን በደንብ እንዲያውቁት መደረጉን ገልጸው፣ ኮርፖሬሽኑ ያሉበትን ብዙ ተግዳሮቶች እንዲፈታ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ሰራተኛውና ማኔጅመንቱ ተደጋግፎ መስራቱ እንዲሁም ዋጋ ለማረጋጋት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል::

 

 photo_1_2024-01-18_09-55-17.jpg  photo_2_2024-01-18_09-55-17.jpg

photo_3_2024-01-18_09-55-17.jpg  photo_2024-01-18_09-58-16_2.jpg

photo_4_2024-01-18_09-55-17.jpg