Kaizen01.jpg
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከካይዘን ልህቀት ማዕከል ጋር የካይዘን ፕሮጀክት ትግበራ የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ሥነ-ሥርዓት መጋቢት 02/ 2016 ዓ.ም አካሄደ፡፡ የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱን አቶ አቻ ደምሴ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና አቶ ለቤዛ አለሙ የካይዘን ልህቀት ማዕከል የአገልግሎት ተቋማት ጥራትና ምርታማነት ማሻሻያ ዘርፍ ም/ ሥራ አስኪያጅ ተፈራርመዋል፡፡


የመግባቢያ ስምምነቱ ከመጋቢት 5/ 2016 ዓ.ም እስከ ነሀሴ 30/ 2016 ዓ.ም ለሚተገበረው ችግር ተኮር ፕሮጀክት መር የአመራር ፍልስፍና የተመረጡ ቁልፍ የኮርፖሬሽኑ ችግሮችን በቀጣይነት ለመፍታት እና የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንዲሁም ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑ ተመልክቷል፡፡


በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ አቶ አቻ ደምሴ ኮርፖሬሽኑ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች ለማስቀጠልና ውጤታማ ለመሆን ካይዘን ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑን ጠቅሰው ከካይዘን ልህቀት ማዕከል የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
አቶ ለቤዛ አለሙ በበኩላቸው የተሻሉ የካይዘን አማካሪዎችን በመመደብና የጋራ እቅድ በማውጣት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጠቁመው የኮርፖሬሽኑ አመራር ለካይዘን ትግበራ ለሚያደርገው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡