9-Months-Performance.jpg
ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተለያዩ ገበያ የማረጋጋት ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ፡-
ለአምራቹ ምርት ገበያ መፍጠር 
ለአርሶ አደሩ ምርት የገበያ ዕድል በመፍጠር ረገድ፡- የአርሶ አደሩን ምርታማነት በቀጣይነት ለመደገፍ ኮርፖሬሽኑ 1,088,387 ኩንታል እህልና 1,691 ኩንታል ቡና እንዲሁም 51,191 ኩንታል ፍራፍሬ እና አትክልት ከምርት አቅራቢዎች ገዝቷል፡፡
ለፋብሪካ ምርቶች የገበያ እድል በመፍጠር ረገድ፡- ኮርፖሬሽኑ ብር 1,332,673,625 ዋጋ ያለው 228,828 ኩንታል ምርት (የፍጆታ ሸቀጥ፣ የስንዴ ዱቄትና ሲሚንቶ) ከሃገር ውስጥ ፋብሪካዎች በመግዛት የገበያ ዕድል ፈጥሯል፡፡
የአቅርቦት እጥረትንና የዋጋ ንረትን ለመከላከል የተደረገ ጥረት
የምርት አቅርቦትን በመጨመር የዋጋ ንረትን ለመቀነስና ገበያውን ለማረጋጋት እንዲቻል ኮርፖሬሽኑ ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለማረሚያ ቤቶችና ሌሎች ሸማች የህብረተሰብ ክፍሎች ብር 136,853,380 ዋጋ ያለው 18,725 ኩንታል ጤፍ፣ ብር 303,071,921 ዋጋ ያለው 47,402 ኩንታል አትክልትና ፍራፍሬ፣ ብር 1,196,046,623 ዋጋ ያለው 11,003,000 ሊትር የምግብ ዘይት፣ ብር 264,509,236 ዋጋ ያለው 38,498 ኩንታል ስኳር፣ ብር 735,275,582 ዋጋ ያለው 86,000 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ ብር 667,267,407 ዋጋ ያለው 86,400 ኩንታል ልዩ ልዩ የፍጆታ ሸቀጦች አሰራጭቷል፡፡
በሌላ በኩል ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀለብ የሚሆን 49,133 ስንዴ እና 86,000 የስንዴ ዱቄት በማቅረብ ሀገራዊ ተልዕኮን ለመወጣት ጥረት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የምርት አቅርቦት እጥረትን ለመሸፈን በተለይም ለአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና ለዓለም ምግብ ድርጅት /WFP/ ብር 242,489,176 ዋጋ ያለው 69,054 ኩንታል በቆሎ ተሠራጭቷል፡፡ በተመሳሳይ በግንባታው ዘርፍ እየገጠመ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረትና ዋጋ መናርን ለመከላከል ከፋብሪካዎች ብር 97,513,425 ዋጋ ያለው 97,179 ኩንታል ሲሚንቶ በቀጥታ በመረከብ ለተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ ማሰራጨት ተችሏል፡፡
የኮርፖሬሽኑ የሸማች ገበያ ማረጋጋት አስተዋፅኦ በገንዘብ ሲመዘን፡-
በዘጠኝ ወራት ውስጥ በነበሩት ልዩ ልዩ ሀይማኖታዊ በዓላት ምክንያት ሸማቹ ማህበረሰብ በርካታ የፍጆታና ሌሎች ሸቀጦች ግዥ በስፋት የሚያከናዉንበት መሆኑን በመገንዘብና አስቀድሞ ዝግጅት በማድረግ ኮርፖሬሽኑ ገበያ ለማረጋጋት የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ልዩ ልዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ያቀረበ ሲሆን የኮርፖሬሽኑ መሸጫ ዋጋ በወቅቱ ከነበረው የገበያ ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በጠቅላላ የብር 1,820,799,021 ቅናሽ ተደርጓል፡፡