የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከኩሽላደር ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ጋር የህንጻ ሙሉ እድሳት (ሪኖቬሽን) የውል ስምምነት ግንቦት 15 ቀን 2016 ዓ/ም አደረገ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ እና የህንጻ እድሳት የሚያከናውነው የኩሽላደር ኮንስትራክሽን ጄነራል ማናጀር አቶ አዲሱ ሞሲሳ የውል ስምምነት ፊርማውን ያከናወኑ ሲሆን ስምምነቱ የዋና መ/ቤት ብሎክ ሁለት ህንጻን ሙሉ እድሳት ለማድረግ የተካሄደ ነው፡፡

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ የህንጻ እድሳቱ ዋና ምክንያት መጪውን ጊዜ የሚመጥን የቢሮ አደረጃጀት እንዲኖርና ለሥራ ምቹ የሆነን ከባቢ ለመፍጠር መሆኑን ጠቁመው፤ የህንጻ እድሳት የሚያከናውነው ድርጅት በጥራትና በጊዜ ስራውን እንዲያከናውን አሳስበዋል፡፡

የኩሽላደር ኮንስትራክሽን ጄነራል ማናጀር አቶ አዲሱ ሞሲሳ በበኩላቸው ድርጅታቸው ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ፈጽሞ የማስረከብ ልምድ እንዳለው ገልጸው፤ የስራ ብቃታቸውን በማሳየት ሌሎች ፕሮጀክቶችንም ከኮርፖሬሽኑ ጋር መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

የህንጻ እድሳቱ በሶስት ምእራፍ የሚከናወን ሲሆን የመጀመሪያው ምእራፍ ከ20 ቀናት በኋላ እንደሚጀመር ይጠበቃል፡፡