የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በጥሬ ገንዘብና በዓይነት በድምሩ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ለመቄዶኒያ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን ማዕከል አደረገ፡፡ የኮርፖሬሽኑ አመራርና ሠራተኞች የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ታህሳስ 24 ቀን 2011 ዓ/ም አዲስ አበባ አያት የሚገኘው ማዕከል በመገኘት አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማንን ጎብኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለመቄዶኒያ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን ማዕከል ያደረገው ድጋፍ በጥሬ ገንዘብ ብር 355,873 ሲሆን ቀሪው በዓይነት በድምሩ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በዓይነት ለማዕከሉ ድጋፍ ያደረጋቸው ምርቶች 100 ኩንታል ነጭ ጤፍ፣ 20 ኩንታል ሽንብራ፣ 40 ኩንታል ስኳር፣ አንድ ካርቶን (368 ፍሬ) ሻይ ቅጠል፣ 7.5 ኩንታል ማካሮኒ፣ 200 ሊትር ዘይት፣ 236 ሊትር ላርጎ ፈሳሽ ሳሙና፣ 18 ባለሁለት ሊትር ፈሳሽ ሳሙና፣ 100 ፍሬ አጃክስ ሳሙና፣ 20 ኩንታል ሙዝ፣ 10 ኩንታል ብርቱካን፣ 240 ጣሳ ማርማላት፣ 995 ጣሳ ቲማቲም ድልህ እና ግምታቸው አስር ሺህ ብር የሆነ ልባሽ አልባሳት ናቸው፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መንግሥቱ ከበደ እና የሠራተኛ ማህበር ተወካዮች ድጋፉን ለማዕከሉ መስራች ክቡር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት አስረክበዋል፡፡ በቀጣይ ማዕከሉን በዘላቂነት ለመደገፍ የኮርፖሬሽኑ አመራርና ሠራተኞች ዝግጁ መሆናቸውን ድጋፉ በተደረገበት ወቅት የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መንግሥቱ ከበደ ገልፀዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የህብረተሰቡን የፍጆታ ዕቃዎችና የምግብ ምርቶች ፍላጎት ለማሟላትና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት የተቋቋመ እንደመሆኑ መጠን ለማዕከሉ የሚያስፈልጉ የእህል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የፍጆታ ዕቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ዘላቂ ድጋፍ ለማድረግ እንደተዘጋጀም ተናግረዋል፡፡