የኢትዮጵያ የንግድ ሥ ራዎች ኮርፖሬሽን በ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና በ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ከደንበኞችና ባለድርሻ አካላት ጋር ህዳር 4 ቀን 2011 ዓ/ም በግሎባል ሆቴል ውይይት አካሂዷል፡፡

በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት አገልግሎት ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታሪኩ በራሱ የምክክር መድረኩን ሲከፍቱ የኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን በ2010 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ገበያ 7.21 ሚሊዮን ኩንታል እህል፣ ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ እና የፍጆታ ዕቃዎች ለመሸጥ አቅዶ 7.77 ሚሊዮን ኩንታል ያከናወነ መሆኑን በ2011 በጀት ዓመት 8.72 ሚሊዮን ኩንታል ለመሸጥ ማቀዱን ገልጸዋል፡፡

የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በበጀት ዓመቱ አሰራሩን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን የመተግበርና የሰራተኞቹን አቅም የሚያጎለብቱ በካይዘን አመራር ፍልስፍና ጽንሰ ሃሳብ፣ በአለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘጋገብ / IFRS /፣ በምርት ጥራትና ክምችት አያያዝ እንዲሁም በውጭ ንግድ ሥርዓት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎች ለኮርፖሬሽኑ አመራርና ፈጻሚዎች መስጠቱን ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡

ለገበያ ማረጋጊያ በኮርፖሬሽኑ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራት ማረጋገጥ፣ ምርቱ መቼ፣ የት እና በማን እንደተገዛ የሚገልፅ ግልጽ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን አቅርቦት ሳይቆራረጥ ለተጠቃሚው ለማቅረብ የኮንትራት ፋርሚንግን አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ፣ የፍጆታ ዕቃዎች ተደራሽነትን ለማሳደግም አቅርቦትና ፍላጎትን ማጣጣም የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ ግዥዎች የመፈጸም አቅምን ማሳደግ በበጀት ዓመቱ ትኩረት የተሰጣቸው ሥራዎች እንደሆኑ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ደንበኞቹና ባለድርሻ አካላት በሚጠብቁበት ደረጃ አገልግሎቱን ለመስጠት እና ባቀደው ዕቅድ ልክ አፈጻጸሙን ለማሳካት በሀገር ውስጥ በሚፈለገው መጠንና ዋጋ የእህል ምርት ገበያው ላይ አለመገኘት፣ በመንግሥት ድጎማ ለገበያ ማረጋጊያ ከውጭ ሀገር የሚገዛውና በኮርፖሬሽኑ የሚሰራጨው የውጭ ስንዴ ግዥ ጨረታ መስተጓጎል ለገበያ ማረጋጊያ ከውጭ ለሚገዙ የፍጆታ ሸቀጥ ምርቶችም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ፍላጎትና አቅርቦቱ አለመመጣጠን፣ ኮርፖሬሽኑ ለውጭ ገበያ የሚቀርባቸው የቡና፣ የቅባት እህልና ጥራጥሬ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የገበያ ዋጋ መብለጥና የምርቶቹ ዋጋ መዋዥቅ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸው በውይይቱ ወቅት ተብራርቷል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ስንዴ ግዥ ጥራት ኢንዱስትሪውን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን እንዲሁም እያጋጠመ ላለው የፍጆታ እቃዎች እጥረት ኮርፖሬሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲፈለግ ጠይቀዋል፡፡ በመድረኩ ላይ እህል አቅራቢ የሆኑ አርሶ አደሮች፣ ህብረት ሥራ ማህበራት፣ ለገበያ ማረጋጊያ ከኮርፖሬሽኑ ስንዴ የሚገዙ የዱቄት ፋብሪካ ባለንብረቶች፣ ከኮርፖሬሽኑ በጋራ የሚሠሩ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች እና ማህበራዊ ተቋማት ተሣትፈዋል፡፡