የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2011 ዓ/ም በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ የቡድን መሪዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ በግምገማው የኮርፖሬሽኑ የእህልና ቡና፣ የፍጆታ ዕቃዎች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የግዥና ማማከር አገልግሎት የንግድ ሥራ ዘርፎች ዕቅድ ክንውናቸውን ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

በእህልና ቡና ንግድ ሥራ ዘርፍ በ2011 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከተለያዩ የሃገር ውስጥ የግዥ ምንጮች 937,034 ኩንታል የብዕር እና የአገዳ እህል፣ ጥራጥሬና ቡና ለመግዛት ታቅዶ 785,481 ኩንታል ግዥ የተከናወነ ሲሆን አፈጻጸሙም 84% ነው፡፡ ሌሎች እህሎች ከመግዣ ዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ግዥ አልተፈጸመም፡፡ ኮርፖሬሽኑ በእህልና ቡና ንግድ ሥራ ዘርፍ በኩል ገበያን ለማረጋጋት ተግባር 1.151 ሚሊዮን ኩንታል ከሀገር ውስጥ ገበያ የስንዴ ግዢ ለማከናወን በ2011 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም በዋጋ መናር ምክንያት በመንግስት እንዳይገዛ በመወሰኑ ግዥ እንዳልተከናወነ በአፈጻጸም ግምገማ ተመላክቷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በሃገር ውስጥና በኤክስፖርት ሽያጭ በ2011 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የገበያ ማረጋጋት ሥራን ጨምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ 5.95 ሚልዮን ኩንታል እህልና ቡና ለመሸጥ አቅዶ 4.25ሚልዮን ኩንታል እህልና ቡና በመሸጥ የዕቅዱን 71 በመቶ መከናወኑ በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል፡፡ 

በዘጠኝ ወራቱ በወጪ ንግድ 70,500 ኩንታል የታጠበ እና ያልታጠበ ቡና ለመሸጥ አቅዶ 29,760 ኩንታል ቡና ለተለያዩ ሀገሮችና ደንበኞች በመሸጥ የዕቅዱ 42 በመቶ የተከናወነ ሲሆን በዘጠኝ ወራት ውስጥ 8,458,602.59 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከቡና ኤክስፖርት ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡ ሆኖም ግን ከ2010 በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ24% ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ 231,071 ኩንታል ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ የአትክልት ዘር፣ የፋብሪካ ምርት፣ ስኳር፣ የሃገር ውስጥ ዘይት፣ ፓልም ዘይትና ሌሎች ለመግዛት ታቅዶ 155,323 ኩንታል (የዕቅዱ 67%) መከናወኑ ተገልጿል፡፡ የግዢ አፈጻጸሙ ከ2010 በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ28% ቅናሽ ያሳየ ሲን ለዚህም በምክንየትነት የተቀመጡት ጉዳዮች መካከል ዋና የፍራፍሬ አቅራቢ ከሆነው ከላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ የሚነሳው የብርቱካን ምርት መቀነስና በበጀት ዓመቱ ከአምስት ያላነሱ ነጋዴዎች ወደ ግብይቱ በመግባት ምርቱን ማንሳት በመጀመራቸው የአቅርቦቱ ማነስ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ዘርፉ በበጀት ዓመቱ በሃገር ውስጥ ሽያጭ 227,057 ኩንታል ተመሳሳይ ምርቶችን ለመሸጥ ታቅዶ 152,692 የተከናወነ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር በመጠን 23% ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በአንጻሩ በውጭ ሀገር ገበያ 9,173 ኩንታል ፍራፍሬ ለመሸጥ ታቅዶ የ4,575 ኩንታል ሽያጭ ማከናወን መቻሉ ተገልጿል፡፡ 

በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች ያሉበት የሥራ ደረጃ በተመለከተ የአትክልት ምርቶች በኮንትራት ለማስመረት ከጂቱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር የአትክልት ምርቶችን በኮንትራት ለማስመረት ውል መፈረሙና ሲሆን ከሰኔ ወር 2011 ዓ/ም ጀምሮ ለገበያ የማቅረብ ሥራ ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ 

በሌላ በኩል የፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ሥራ ዘርፍ በበጀት ዓመቱ 637,336 ኩንታል የተለያዩ የፍጆታ ዕቃወችን ለመግዛት አቅዶ 358,701 ኩንታል ማከናወኑና የግዥ አፈጻጸሙ ከ2010 በጀት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ29% በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቅሷል፡፡

የግዥ ሥራዎችን እና አቅርቦት በተመለከተ በዘጠኝ ወራቱ አዳዲስ 46 በምርትና በአይነት የተለያዩ ምርቶች ከሀገር ውስጥ ተገዝተው መቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን በአዲስ ከቀረቡት ውስጥ 26 ዓይነት ምርቶች ቀድመው ይቀርቡ የነበሩ ነገር ተቋርጠው የነበሩና በአዲስ ውልና ድርድር የቀረቡ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል 14 አዳዲስ አምራቾችን ወደ ድርጅቱ ማምጣት መቻሉ የተገለጸ ሲሆን በአጠቃላይ 637,336 ኩንታል ምርት ለመሸጥ ታቅዶ 448,632 መሸጡ ተገልጿል፡፡

በግዥና ማማከር አገልግሎት ዘርፍ በዘጠኝ ወራቱ የ580 ሚሊዮን ብር የአገልግሎት ግዥ የተከናወነ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ በገቢ ይመዘገባል ተብሎ ከታቀደው ብር 10.59 ሚሊዮን ውስጥ የተከናወነው ብር 8.37 ሚሊዮን መሆኑ ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በሪፖርት ወራቱ ከምክርና ሥልጠና ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ከነበረው ብር 1.3 ሚሊዮን ውስጥ ለተለያዩ 306 መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ለተውጣጡ ሠልጣኞች የግዥ ሥልጠና በመስጠት ብር 1.24 ሚሊዮን ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ 12,377,636.32 ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 9,693,563.23 መከናወኑ ተመልክቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማ ተሣታፊዎች በቡድን ባካሄዷቸው የቡድን ውይይቶችና የተገመገሙ ሲሆን  የታዩ ችግሮችና የመፍትሔ ሃሳቦች በስፋት ቀርበዋል፡፡ ከተነሱ አበይት ችግሮች መካከል የውጭ አገር ሽያጭ መቀዛቀዝ፣ በአንዳንድ የግብይት ሰብሎች (ለምሣሌ ኑግ፣ በቆሎ፣ ሽምብራ) የሀገር ውስጥ የመግዣ ዋጋ ከውጭ አገር መሸጫ ዋጋ መብለጥና ከፍተኛ የሆነ የምርት ክምችት መኖር፣ የመግዣና መሸጫ ዋጋ ውሳኔ የተማከለ መሆን እና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበት አካሄድ አለመኖሩ፤ የገበያ ማፈላለግ ሥራ በአንጻራዊነት ደካማ መሆን፤ በኮርፖሬሽኑና በዘርፉ መካከል የሥልጣንና ሀላፊነት ግልጽነት ጉድለት መታየቱ፤ በበሀብት አጠቃቀም እና ንብረት አስተዳደር ላይ ችግር መኖሩ፤ የተሟላ የኢንሹራንስ ሽፋን አለማግኘት፤ በግዥና በሽያጭ ደንበኛን የማፈላለግና የማቆየት ችግር ነባር ደንበኞች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በዘርፉ በመፍትሔ አማራጭነት ከተቀመጡት ሃሳቦች መካከልም እሴት ጨምሮ መሸጥ ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ፤ የግብይት ሥራዎች በተሻለ ውጤታማ እንዲሆኑ ኮርፖሬሽኑ የገበያ ማፈላለግ ሥራን ከሌሎች አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚያስፈልገው፤ ሀብትና ንብረቶች ይበልጥ በተደራጀ አኳኋን አግባብነት ያለው ባለቤት ተፈጥሮላቸው እንዲ ተዳደሩ ማድረግ፤ የመጋዘን ጥገና ሥራዎች በወቅቱ ተከናውነው የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ 

በተመሣሣይም በአትክልትና ፍራፍሬ የንግድ ሥራ ዘርፍ ክንውን ላይ የተለያዩ ጉዳዮች በተሣታፊዎች የተዳሰሱ ሲሆን፤ የኮንትራት ፋርሚንግ ሥራ ተጠናክሮ አለመቀጠሉ፤  የምርት አቅራቢዎች ቁጥር ውስን መሆኑ፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፤ በአንዳንድ የሽያጭ ሠራተኞች ላይ የሥነ ምግባር ችግር መታየቱ፤ የምርት ብልሽትን አስቀድሞ የመከላከል ችግር ሙሉ ለሙሉ አለመቀረፉ እንደ ችግር የተነሱ ሲሆን የመሸጫ ሱቆችን ማዘመን፤ የተለያዩ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎችን በማከናወን የአቅራቢዎችን ቁጥር መጨመር፤ አቅም ካላቸው የክልል አምራቾች ጋር የገበያ ትስስር መፍጠር፤ ህገ-ወጥ ንግድን ከሚመለከተው ጋር በመሆን እንዲፈታ ጥረት ማድረግ፤ ከሌሎች ዘርፎች ጋር በተሻለ ተቀናጅቶና ተናብቦ መሥራት በሚሉት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ 

ከፍጆታ ሸቀጦች ንግድ ሥራ ጋር በተያያዘም በተለይም በአለ በጅምላ በብድር የተወሰደው ገንዘብ እንዲመለስ ኮርፖሬሽኑ ከሌሎች ጋር በመተባበር እንዲፈታ ማድረግ እንዲሁም ለፍጆታ አቃዎች በብድር የተሰጠ ገንዘብ እንዲመለስ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ ሃሳብ ቀርቧል፡፡ 

በተጓዳኝ የሥራ ሂደቶች ክንውን ዙሪያ በተደረጉ የቡድን ውይይቶች ከተነሱ አንኳር ጉዳዮች መካከል ከጅንአድ የተዛወረ 8000 ካ/ሜ መካዝን ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረግ፤ የምርት ሥርጭት /በተለይም ወደ መዳረሻ የሚሄዱ ሸቀጦች/ በተሻለ ጥራት እዲከናወን ማድረግ፤ የሂሳብ ምርመራዎች በወቅቱ እንዲካሄዱ ማድረግ፤ የውጤት ተኮር ሥልጠና በተለይ በሥራ አመራሩ ውስጥ ሊያሰርጽ በሚያስችልበት አኳኋን እንዲካሄድ ማድረግ፤ የለውጥ መሳሪያዎች በአውቶሜሽን እንዲደገፉ ማድረግ፤ የኮርፖሬት አስተሳስብን የመፍጠር ሥራዎች ደካማ በመሆናቸው በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ ማከናወን፤ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን በተሻለ ጥራትና ወቅታዊነት እንዲከናወኑ ማድረግ፤ ለህግ ከቀረቡ ጉዳዮች መካከል 60 በመቶ በማሸነፍ ቀሪው 40 በመቶ ደግሞ በሽነፈት የተጠናቀቁ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሽንፈቶቹ መሠረታዊ ምክንያቶች ተለይተው ተገቢው የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ፤ በክርክር ላይ በሽንፈት ምክንያት የሚመጣውን ኪሳራ ለማስቀረት ቅድመ መከላል ላይ ማተኮር፣ የማማከር እንዲሁም ጉዳዮችን በድርድር የመፍታት አቅምን ማዳበር በሚሉት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት እንዳለበት ተጠቅሷል፡፡  በመጨረሻም በተነሱ ጉዳዮች ላይ በአመራሩ ሰብሳቢነት አጠቃላይ ውይይት ተደርጎ የግምገማ መድረኩ ተጠናቋል፡፡