addis.jpg
አዲስ አበባችን ለረጅም አመታት በመዝናኛ ቦታዎች እጥረት ነዋሪዎቿ ሲወቅሷት ኖረዋል:: ከተሞች የቱንም ያህል በመሰረተ ልማት ቢለሙም በወንዝ ዳርቻዎች የሚካሄድ ልማት ከሚሰጠው የአእምሮ እርካታ አንጻር እምብዛም ነው፡፡ በእኛም ሀገር ሁኔታ በወንዞችና ሀይቆች ዙሪያ የተመሰረቱ ከተሞች ምን ያክል ነዋሪዎቻቸውን አለፍ ሲልም ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ጎብኝዎችን አእምሮ እንደሚያዝናኑ ግልጽ ነው፡፡ መዲናችን አዲስ አበባ ጸጋው እያላት ጸጋዋን ሳታለማና ሳትጠቀምበት ለረጅም ግዜ ቆይታለች፡፡ አሁን ግን ለረጅም ጊዜ የቆሻሻ መጣያ ሆነው የከረሙ ወንዞቿን ለማልማት ቆርጣ ተነስታለች፡፡
ከእንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ ከተማዋን ለሁለት ከፍለው በሚፈሱ ወንዞች ግራና ቀኝ የሚሰራው የወንዝ ዳርቻ ልማት የተግባር እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ልማቱ 51 ኪ/ሜ ርዝመት የሚሸፍን ሲሆን በ29 ቢሊዮን ብር ወጭ ይከናወናል፡፡ የወንዝ ዳርቻው ልማት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠሩም በላይ ከተማዋን ጽዱና ማራኪ በማድረግ በኩል ድርሻው የጎላ ነው፡፡ የወንዝ  ዳርቻ ልማቱ ሲጠናቀቅ መዲናችንን እንደ ስሟ አዲስ አበባ ውብ እና ማራኪ በማድረግ የቱሪዝም መስኩን የበለጠ በማነቃቃት በኩል ልዩ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በሳምንቱ መጨረሻ በስራ ደክሞ የሰነበተ አእምሯቸውን ዘና ለማድረግ ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚጓዙ የከተማዋ ነዋሪዎች መልካም አጋጣሚ ይሆንላቸዋል፡፡ በዚህም ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን እንዲሁም ድካማቸውን መቀነስ ያስችላቸዋል፡፡  ከዚህም በተጨማሪ በየእለቱ በትርፍ ሰዓታቸው መዝናናት ለሚፈልጉ የመዲናዋ ነዋሪዎች እንደ መዝናኛ አማራጭ ከመሆኑም ባሻገር ከተማዋን ጽዱና ማራኪ በማድረግ በኩል ድርሻው የጎላ ነው፡፡ 
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሚያደርጋቸው ተሳትፎዎች የዳበረ ልምድ ባለቤት ነው፡፡ በማህበራዊ ጉዳዮች በመሳተፍና ድጋፍ በማድረግ በጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ግንባር ቀደም ተሳትፎ ያለው ኮርፖሬሽኑ በ “ሸገርን ማስዋብ” እቅድ ላይም ያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ የወንዝ ዳርቻ ልማት ከግብ እንዲደርስ ባለድርሻ አካላት ርብርብ በማድረግ ላይ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን 250¸000 ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገባ ሲሆን በቀጣይም አጋርነቱን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኑ ታውቋል፡፡ በእርግጥም ሸገርን ማስዋብ ትኩረት ሊነፈገው የማይገባው ጉዳይ መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡