Algeria01 01.jpg
 
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአልጄሪያ በተካሄደው 52ኛው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ ተሣትፏል፡፡ ከሰኔ 15-20/2011 ዓ/ም በአልጄሪያ ዋና ከተማ አልጀርስ በተካሄደው በዚሁ የንግድ ዓውደ ርዕይ ላይ የኮርፖሬሽኑ የእህልና ቡና ንግድ ሥራ ዘርፍ በአዲስ አበባ የንግድ ምክር ቤት አስተባባሪነት ከሦስት የግል ቡና አምራች ድርጅቶች እንዲሁም ቆዳ አምራቾች ጋር በመሆን የመጀመሪያውን ተሣትፎ አድርጓል፡፡ በትርዒቱ ላይ የኢትዮጵያን የቡና መገኛነት፣ አገሪቱ የምትታወቅበትን የኮፊ አራቢካ የቡና ዙርያ ተመራጭነትና ባህሪ ለተሣታፊዎች ማስተዋወቅ የተቻለ ሲሆን፤ አገሪቱ በዓለም ዓቀፉ የቡና ምርት ግብይት ውስጥ የሚኖራትና ተሣትፎና ድርሻ በተለይም የደንበኞችን ቁጥር ለመጨመርና የኮርፖሬሽኑን ምርቶች ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ ግንኙነቶችና ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ 
 
አልጄሪያ በዓለም ላይ ቡና ተጠቃሚ ከሆኑ አገሮች አንዷ ሰትሆን በያዝነው የፈረንጆች ዓመት 76 ሺህ ሜትሪክ ቶን ቡና ከውጭ አስገብታለች፡፡ ይሁን እንጂ በዓለም ላይ በጣዕሙም ሆነ በጥራቱ ተመራጭ የሆነ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የምትታወቀው አገራችን ከዚህ ገቢ ምርት ውስጥ የነበራት ድርሻ 19 ሜትሪክ ቶን ወይም ከ1 በመቶ ያነሰ ሆኖ መገኘቱ በቡና ወጪ ንግድ ላይ ድርሻን ተሣትፎን እጅጉን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አመላክቷል፡፡
 
በአሁኑ ወቅት በቡና ወጪ ንግድ ዘርፍ የሚታዩ ተግዳሮቶች እየጠነከሩ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ቀስ በቀስ ከገበያ የመውጣት ስጋቶችን ከወዲሁ ማስቀረት ከመቻል አኳያ በንግድ ትርዒቱ ላይ ከተደረገው ተሣትፎ የተወሰዱ ግንዛቤዎች አዎንታዊ ሚና እንደነበራቸው ተገልጿል፡፡ 
 
አልጄሪያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ድጋፍ ሰጪነት በተዘጋጀ መድረክ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት በተለይም ከቡና አስመጪዎችና ኢንቬስተሮች ጋር መገናኘትና በተለያዩ የንግድ ማሻሻያ ጉዳዮች ላይ ገንቢ ውይይት ማድረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡ ለአብነትም በአልጄሪያ የብራዚል አምባሳደርን ጨምሮ ከሌሎች አገሪቱን ወክለው በንግድ ትርዒቱ ላይ የተገኙ ተሣታፊዎች የአገራችን የቡና ምርት የጎበኙ ሲሆን በተመሳሳይም ኢትዮጵያን ወክለው የተሣተፉ ባለሙያዎች የብራዚል ምርቶችን በመጎብኘት ጠቃሚ ግንዛቤዎችን መወሰድ ችለዋል፡፡ 
 
 
ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ማቅረብ የምትችለው ቡና በጥራቱ ከፍተኛና ተፈላጊ ሆኖ ሳለ ሌሎች አምራች አገራት ከዚህ ያነሰ ጥራት ያለው ምርት ይዘው የተሻለ ገበያ ማግኘት መቻላቸው አገሪቱ በንግዱ ዘርፍ ልትፈታቸው የሚገቡ ጉልህ ክፍተቶች መኖራቸውን ከዓውደ ርዕዩ  ተሣትፎ መረዳት ተችሏል፡፡ በተለይም በአገር ውስጥ የሚቀርበው የቡና ምርት የመግዣ ዋጋ ከዓለም የገበያ ዋጋ በእጥፍ ከሚልቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኤክስፖርተሮች ከዓለም ገበያ ውጭ መሆናቸው፤ የቡና ምርት ከአገር ውስጥ ገበያ ከተገዛበት በታች በሆነ ዋጋ ሲሸጥ በሚመለከተው አካል እርምጃ አለመወሰዱ ወይም የወጪ ንግድ የዋጋ ወለል መሰን አለመቻሉ በዓለም አቀፉ ገበያ ላይ በሚፈለገው ልክ ተወዳዳሪ ሆኖ ላለመውጣት ምክንያት መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ 
 
በአልጄሪያ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት ከአልጀሪያ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ጋር በመተባበር ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ጠቃሚ የB to B የንግድ ውይይት በጥልቀትና በተናጥል በማድረግ በቀጣይ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የሥራ ግንኙነት ለመጀመር ከሚችሉ ደንበኞች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት ንግድ ትርዒቱ ላይ ለመሳተፍ ከመጡ የብራዚል ኤክስፖርተሮች ጋር በአምባሳደራቸው በኩል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ተችሏል፡፡ 
 
በሌላ በኩል ጥራጥሬ ፣ ቅባት እህል፣ ቅመማ ቅመም እና ቡና ኢምፖርት ለማድረግ የሚፈልጉ አስመጪዎች ፍላጎታቸውን የገለፁ ሲሆን፤ ነገር ግን የአገሪቱ የአቅርቦት ዋጋ ከፍ ያለ በመሆኑ በወቅቱ ካለው ዓለም አቀፍ ዋጋ አንፃር እጅግ ውድና አዋጪ አለመሆኑን በመግለፅ ስምምነት ላይ ለመድረስና ውል ለመዋዋል ሳይቻል ቢቀርም ቀጣይ ግንኙነቶችን በማድረግ የንግድ ግንኙነቶችን ለማሳካት ጥረት የሚደረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
እነዚህ ችግሮች መፈታት ከቻሉ ኮርፖሬሽኑ የንግድ ዘርፉን ለማጎልበት ካለው አቅም ጋር ተዳምሮ በቀጣይ የቡና ምርት ግብይትን ማጎልበት የሚቻል መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በተለይም የቡና ምርትን በፍሬ ደረጃ ለገበያ ከማቅረብ ባሻገር የአገሪቱን የተለያዩ የቡና ዝርያዎች የዓለም አቀፉ ገበያ በሚፈልገው ዓይነት በፋብሪካ አቀነባብሮ እሴትን በመጨመር በቀጥታ ለተጠቃሚዎች ፍጆታ ማቅረብ መቻል በዘርፉ በተሻለ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚረዳ ከዓውደ ርዕዩ  ተሞክሮ መገንዘብ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ በዘርፉ የሚታዩ የገበያና የግብይት ችግሮችን ከባለድርሻ አጋራት ጋር በመሆን ለመፍታት በመንቀሳቀስ የንግድ ዘርፉን ለማሳደግ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
 
በዓውደ ርዕዩ ላይ ፈረንሣይ፣ ስፔይን፣ ብራዚል፣ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት፣ ካናዳ፣ ማሊ፣ ሴኔጋልና ሌሎችም በቡና ምርትና ንግድ ግንባር ቀደም ሥፍራን የያዙ አገራትና ኩባንያዎች ተሣትፈዋል፡፡
Algeria02 02.jpgAlgeria03 03.jpg