Planting01.jpg

ደን ህይወት ነው፡፡ አዎ በእርግጥም ደን ህይወት ነው፡፡ ዓለማችንን እያስጨነቀ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤው የደን መመናመን ነው፡፡ ምድራችን ያለደን ውበት የላትም፡፡ ደን ስትለብስ ግን ግርማ ሞገሷን ትላበሳለች፤ እስትንፋሷም ይስተካከላል፡፡

 

ዕጽዋት የከተማችንን የአየር ንብረት ለመጠበቅም ሆነ አካባቢን ለማስዋብ ያላቸው ጠቀሜታ የጎላ ከመሆኑ አንጻር ችግኞችን መትከል የተተከሉትን ተንከባክቦ ማሳደግ ለአካባቢ ጥበቃ መሠረት ነው፡፡ በያዝነው በጀት አመት አረንጓዴ አሻራ እናሳርፍ፤ በአንድ ጀምበር 200 ሚሊየን ችግኝ እንትከል!” በሚል መሪ ቃል በመላ ሀገሪቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ መርኃ ግብሩ በዋናነት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ/ም የሚከናወን ሲሆን እንቅስቃሴው ቀድሞ ተጀምሯል፡፡ ይህ መርኃ ግብር የሀገሪቱን የደን ሽፋን ትርጉም ባለው መልኩ አንድ እርምጃ ወደ ፊት የሚያራምድ መሆኑ በብዙዎች ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

 

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ይህንን ሀገራዊ አጀንዳ ተቀብለው ሀምሌ 6 ቀን 2011 ዓ/ም ሳሪስ በሚገኘው የኮርፖሬሽኑ የእህል ማከማቻ ቅጥር ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሂደዋል፡፡

 

በችግኝ ተከላው ወቅት የኮርፖሬሽኑ ኮርፖሬት ሰርቪስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታሪኩ በራሱ መርሃ ግብሩን አስመልክተው ደን ከሰው ልጆች ህይወት ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለውና ከደማችን ጋር የተያያዘ መሆኑን በመጥቀስ ንጹህና ያልተራቆተ አካባቢን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ያሳሰቡ ሲሆን ችግኞችን መትክል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትም እንዲጸድቁ ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ በመጠቆም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ በአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሙ የችግኝ ተከላን በዋና መሥሪያ ቤቱና በክልል የግብይት ማዕከላት የነደፈ ሲሆን የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የአካባቢ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡

 

ዘንድሮም የተሣተፉት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በዕለቱ የተተከሉትን ችግኞችም ሆነ የቀደሙትን ተንከባክበው ለፍሬ እንደሚያበቁ በችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ላይ ቃል ገብተዋል፡፡