Cement

 

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአገራችን በግንባታው ዘርፍ ማነቆ ሆኖ የሚገኘውን የሲሚንቶ ዋጋ ንረትና የምርት እጥረት ለማረጋጋት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ምርቱን እንደዲያከፋፍሉ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ/ም በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተደረሰው ውሳኔ መሠረት ምርቱን ከአገር ውስጥ አምራቾች በመግዛት በኮንስትራክሽን ሥራ ለተሠማሩ አካላት ማከፋፈል ጀምሯል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ የሲሚንቶ ምርትን በቀጥታ ከአምራች ፋብሪካዎች በተለይም በዋነኝነት ከዳንጎቴ፣ ደርባና ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በመግዛት ለአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ ለጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ለአዲስ አበባ አስተዳደር ለሚገኙ የመንግሥት ፕሮጀክቶች፣ ለክፍለ ከተሞችና በግንባታው ለተሠማሩ ሌሎች አካላት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

 

በአገራችን እየተከሰተ ባለው የሲሚንቶ ዋጋ ንረት ምክንያት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳ እንደሚገኝና ይህንን ለማስተካከል በንግድና ኢንዱስትረ ሚኒስቴርና በሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች መካከል ውይይቶች ሲደረጉ ቢቀይም ችግሩ ሊፈታ ካለመቻሉ በተጨማሪ በአንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የሲሚንቶ ምርት እጥረት እየተከሰተ መሆኑን ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጀ ያመለክታል፡፡

 

በመሆኑም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከአምራች ፋብሪካዎች፣ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሲሚንቶ ምርትን በቀጥታ ከፋብሪካዎች በመግዛት እንዲያከፋፍሉ፤ አምራች ፋብሪካዎችም የሲሚንቶ ምርታቸውን በቀጥታ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንዲሸጡ በወሰነው መሠረት ነው ኮርፖሬሽኑ የማከፋፈል ሥራውን እየከወነ የሚገኘው፡፡

 

እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2012 ድረስ ባለው ጊዜ ከ90 ሺህ በላይ ኩንታል ሲሚንቶ ለምርት ፈላጊዎች መከፋፈሉን ከሽያጭ ክፍሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡