Tree Planting 2012 EC s

በክረምት ወራት ችግኞችን በመትከል የተራቆተውን የአገራችንን የደን ይዞታ የመመለሱ ተግባር ላለፉት በርካታ ዓመታት በአገራችን ሲተገበር መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ በመጣው ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖና የበርሃማነት መስፋፋት ምክንያት ትገበራው የተፈለገውን ውጤት ሳያመጣ ቆይቷል፡፡ ይህን ከግንዛቤ በማስገባት መንግሥት በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ አገራዊውን የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በጎለበተና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባተፈ መልኩ “የዜጎች የአረንጓዴ አሻራ ቀን እናሳርፍ፤ በአንድ ጀንበር 200 ሚሊየን ችግኝ እንትከል!” በሚል መርህ በአገር አቀፍ ደረጃ 4 ቢሊየን ችግኞች እንዲተከሉ ተደርጓል፡፡

 

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንም ሁሉንም ሠራተኞቹን በማስተባበር በድምሩ 12 ሺህ ያህል ችግኞች በመትከልና በመንከባከብ ለአገራዊ ግቡ መሣካት የራሱን አስተዋጽዖ ማድረጉና የታሪክ አሻራ ባለቤት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ዘንድሮም “5 ቢሊየን ዛፎች ለአረንጓዴ ኢትዮጵያ፡ አረንጓዴ አሻራችንን ማሳረፋችንን እንቀጥላለን” በሚል መርህ እየተካሄደ በሚገኘው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር አካልነት ሐምሌ 4 ቀን 2012 በሁሉም የኮርፖሬሽኑ ማዕከላት ቡድን በተደራጁ ሠራተኞቹ አማካኝነት የችግኝ ተከላ አካሂዷል፡፡

 

መርኃ ግብሩ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በሎጂስቲክስና የቴክኒክ አገልግሎት ቅጥር ግቢ የተጀመረ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ የኮርፖሬሽኑ ግቢዎች ማለትም በፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና  መ/ቤትና መገናኛ ቅርንጫፎች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ወና መ/ቤት፣ በአቃቂ፣ በእህልና ቡና ንግድ ዘርፍ የቡና ማደረጃና ማከማቻ ማዕከል፣ በአደይ አበባ ግቢና በአዲስ አበባ ዙሪያ ግብይት ማዕከል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ፣ አካባቢ ጥበቃ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጾ ያላቸውንና ለውበት የሚያገለግሉ 1500 ያህል ችግኞች ከ450 በላይ ሠራተኞችን በማሳተፍ ተከላው ተካሂዷል፡፡ በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ ቀሪዎቹ የኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ መ/ቤቶች 10 ሺህ ችግኞችን የማስተከል ሥራዎች ከወዲሁ ተጀምረዋል፡፡

 

በቀዳሚው ዓመት የተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሠራተኛው ዘንድ ጥሩ መነሳሳትንና እንደ አገር ለአረንጓዴ ልማት ያለውን ጠቀሜታን በተመለከተ ግንዛቤን የፈጠረ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህ ዓመትም ከችግኝ ተከላ በኋላ በሚዘጋጀው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም የመንከባከብ ሥራ እንደሚከናወንና በዚህም የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጁነት መኖሩን ተገልጧል፡፡

 

ለአትክልትና ፍራፍሬ ዛፎች ልዩ ትኩረት በተሰጠበት በዘንድሮው የተከላ ፕሮግራም ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ብቻ 300 የአቮካዶ፣ 350 የማንጎ፣ 210 የዘይቱንና 220 የሎሚ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን 710 የጃካራንዳና 210 የሚሊያ ዛፍ ችግኞች ተከላም ተከናውኗል፡፡ የእንክብካቤ ሥራዎችም ለአፈጻጸም በሚያመች መልኩ ሠራተኛውን በየሥራ ክፍሉ በቡድን ተከፋፍሎ የሚያከናውኑበት አሠራር መመቻቸቱን ታውቋል፡፡