Palm_Oil2.JPG

ታህሣሥ 25/2015 ዓ.ም - ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የምግብ ዘይት አንዲያገኝ በጅቡቲ ከሚገኘው ጎልደን አፍሪካ ካምፓኒ የ43 ሚሊዮን 37 ሺ 412 ሊትር የፓልም የምግብ ዘይት ግዢ መፈጸሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አሰታውቋል፡፡

የግዢ ውሉን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ሲሆኑ ለግዢ የሚውለውን የ69 ሚሊዮን 894ሺ 440 የአሜሪካን ዶላር ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋስትና የሰጠው የገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑ ታወቋል፡፡

የምግብ ዘይቱ ግዢ በአንድ አመት የክፍያ ጊዜ የሚፈጸም ሲሆን ይህን የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ዋጋን ለማረጋጋት ታስቦ የተፈጸመውን ግዢ ያስተባባረው የገንዘብ ሚኒስቴር የግዢ ውሉን ለተፈራራሙት ለኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅቶች በላከው ደብዳቤ በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ እሽግ የፓልም ምግብ ዘይት የመሸጫ ዋጋ እንደሚከተለው አሳውቋል፡-

የአዲስ አበባ የፓልም ምግብ ዘይት መሸጫ ዋጋ
• ባለ 3 ሊትር በጄሪካን …… ብር 314
• ባለ 5 ሊትር በጄሪካን …… ብር 510
• ባለ 20 ሊትር በጄሪካን …… ብር 2003 መሆኑ ታውቋል

ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ከተሞችን በተመለከተም ርቀትን ታሳቢ በማድረግ የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ ታሪፍ በኩንታል 60 ሳንቲም በአንድ ኪ.ሜ መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ ሽያጭ እንዲከናወንና የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርም በተለመደው መልኩ የክልልና የከተማ አስተዳደሮችን የስርጭት ኮታ በመመደብ ለኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት እዲያሳውቅ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

(የገንዘብ ሚኒስቴር)

Training_2.jpg

የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽንን በቅርቡ ለተቀላቀሉ አዲስ ሰራተኞች የትውውቅ ስልጠና ታህሳስ 13 ቀን 2015 ዓ/ም ተካሄደ፡፡ ስልጠናውን ያዘጋጀው የኮርፖሬት የሰው ሃብት ልማትና ሥራ አፈጸጻም አመራር ቡድን ሲሆን የስልጠናው ዓላማ ለአዲስ ሰራተኞች የኮርፖሬሽኑን አጠቃላይ ገጽታ እና አሰራር ማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በኮርፖሬሽኑ የሰው ሃብት ልማትና ሥራ አፈጸጻም አመራር ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ይመር አዲስ ሰራተኞች ኮርፖሬሽኑን ሲቀላቀሉ ስለድርጅቱ አወቃቀር፣ የሥራ ሂደት እንዲሁም ከሥራ ባልደረቦች ጋር የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ገልጸው በዚህም መሰረት የዛሬው ስልጠና መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ምክረ ተክሌ፣ ከፍተኛ የሰው ሃብት ባለሙያ በኮርፖሬሽኑ የህብረት ስምምነትና በሃብት አመራር መመሪያ ላይ የተቀመጡ የሰራተኞች መብትና ግዴታዎችን ለአዲስ ሰራተኞች ያብራሩ ሲሆን አዲስ ሰራተኞች በመመሪያ የተደገፉ መብትና ግዴታቸውን አውቀው መስራት እንደሚገባቸውና በተቻለ መጠን የሥራ ዲሲፕሊን ጠብቀው መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

Acha_Message_New_Year.jpg

photo_2022-11-04_15-15-58.jpg

 

ኮርፖሬሽኑ ከዋና መ/ቤት ጀምሮ በሁሉም ዘርፎችና የክልል ግብይት ማእከላት ለሚገኙ የሥራ ሃላፊዎች እና ሰራተኞች የ2014 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2015 በጀት ዓመት የእቅድ ትውውቅ የማጠቃለያ መድረክ በአዳማ ከተማ ከጥቅምት 19-20/ 2015 ዓ.ም አድርጓል፡፡ ከማጠቃለያ መድረኩ አስቀድሞ በአዲስ አበባ (በሁለት ዙር)፣ በአዳማ፣ በሃዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በደሴና በባህር ዳር ተመሳሳይ መድረኮች ተካሂደዋል፡፡

በማጠቃለያ መድረኩ ላይ የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚዎችና የዘርፎች ሥ/ አስፈጻሚዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ የጽ/ ቤት ኃላፊዎችና የአራቱ ንግድ ስራ ዘርፎች በየደረጃው ያሉ የሥራ ሃላፊዎች እስከ ከፍተኛ ባለሙያ ተገኝተዋል፡፡ የውይይቱ ዋና ዓላማ በበጀት ዓመቱ ታቅደው የነበሩ ስራዎችን ክንውን በመገምገም የነበሩ ጥንካሬዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የታዩ ችግሮችን ከምንጩ ለይቶ በ2015 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸምን አስመልክቶ በቀረበው ሪፖርት የመሠረታዊ ፍጆታ አቅርቦት /ግዥ/ የምርት ስርጭትና ተደራሽነት /ሽያጭ/ አፈፃፀም የአቅርቦት እጥረትንና የዋጋ ንረት ለመከላከል የተደረገ ጥረት በዝርዝር ቀርቦ አፈጻጸሙ ላይ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የ2015 በጀት ዓመት እቅድን አስመልክቶ እቅዱ ሲዘጋጅ በየዘርፉ የቀረበውን ፍላጐት አቅምን ያገናዘበና ተልዕኮን ለማሳካት ቅድሚያ ትኩረት የሚሠጣቸውን በመለየት የተሰራ መሆኑን፣ ያለፉት በጀት ዓመታት ዕቅድ አፈፃፀም እንደ መነሻ በታሳቢነት የተወሰዱ መሆናቸው እና ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ የሁኔታ ትንተናዎች ግምት ውስጥ መግባታቸው በቀረበው ገለጻ ተመላክቷል፡፡ እቅዱ በዋነኛነት የገበያ ማረጋጋት ሥራን እና የገበያ ድርሻን በማሳደግ ዋናውን የኮርፖሬሽኑን ተልዕኮ ለማሳካት የሚያስችል እንዲሆን ታስቦ መዘጋጀቱ በገለጻው ተጠቅሷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ እቅዱ ከያዛቸው ዋና ዋና ግቦች መካከል የግዢ ዕቅድን ስንመለከት በ2015 በጀት ዓመት ከተለያዩ የግዢ ምንጮች 3,102,318 ኩንታል ምርት በብር 11,104,108,556 ለመግዛት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን የሽያጭ ዕቅድን በተመለከተ ደግሞ ኮርፖሬሽኑ በ2015 በጀት ዓመት የማረጋጋቱን ሥራ ጨምሮ በአገር ውስጥ እና በወጪ ግብይት ብር 12,674,763,285 ዋጋ ያለው ምርትና አገልግሎት ለመሽጥ ዕቅድ ይዟል፡፡ ከዚህ ውስጥ የሀገር ውስጥ ሽያጭ 12,069,480,785 ብር እና ኤክስፖርት ሽያጭ 605,282,500 ብር ይይዛሉ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ በማጠቃለያ መድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በ2015 በጀት ዓመት እቅድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ሁሉንም አቅም በመጠቀም የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለው ከጠቀሷቸው ተግባራት መካከል የግዢ አፈጻጸም ትስስር፣ የደንበኞች አያያዝ፣ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንዲሁም የሥራ አፈጻጸም አሞላልና ነጥብ አሰጣጥ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ኦፕሬሽናል ልቀት፣ የመፈፀም እና ማስፈፀም አቅም፣ የማያቋርጥ ለውጥና ተወዳዳሪነት እንዲሁም ስትራቴጂያዊ አጋርነት የኮርፖሬሽኑ የትኩረት መስኮች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

cement-1771678.jpg

መንግስት ከሲሚንቶ ምርት ግብይት አኳያ የሚታየውን ችግርና የዋጋ ንረት ለማረጋጋትና የምርት ስርጭቱን ቅደም ተከተል በማስቀመጥ ግብይቱን ግልጽና ተደራሽ ለማድረግ እንዲያስችል የአሰራር ስርዓት ዘርግቷል፡፡ በመሆኑም ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በተላከው የሲሚንቶ ምርት፣ ግብይትና ስርጭት መመሪያ መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ለሲሚንቶ ምርት ፈላጊዎች ሽያጭ እያከናወነ ይገኛል፡፡

አስፈላጊውን መረጃ ላሟሉ ለመንግስት ግንባታ እና ለግል ገንቢዎች እንዲሁም ለብሎኬት አምራቾች ከነሐሴ 17/ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሆነ የሽያጭ ፕሮግራም ኮርፖሬሽኑ ያወጣ ሲሆን ተጠቃሚ የሚሆኑት ክፍለ ከተሞች ቂርቆስ፣ ልደታ፣ አዲስ ከተማ፣ ኮልፌ ቀራንዮ፣ ጉለሌ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ናቸው፡፡ ከነሐሴ 17- 27/2014 ዓ.ም የቂርቆስ፣ የልደታ እና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ተጠቃሚ የነበሩ ሲሆን ከነሐሴ 28/ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ የጉለሌ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ደግሞ በመቀጠል በወጣላቸው ፕሮግራም መሰረት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡