Evaluation.jpg

 

የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የበጀት ዓመቱ እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ከነሐሴ 2-4/ 2014 ዓ.ም የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የዘርፎች ሥ/ አስፈጻሚዎችና እስከ ቡድን መሪ ያሉ የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ ለሶስት ቀናት የተካሄደው መድረክ ዓላማ፣ በበጀት ዓመቱ ታቅደው የነበሩ ስራዎች ክንውን በመገምገም የነበሩ ጥንካሬዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የታዩ ችግሮችን ከምንጩ ለይቶ መፍትሄ በማስቀመጥ በ2015 በጀት ዓመት ውጤታማ ስራ ለመስራት ነው፡፡

በውይይቱ ለህብረተሰቡ በገበያ ማረጋጊያነት የሚቀርቡ መሰረታዊ የምግብ እህል ምርቶች፣ የፍጆታ ሸቀጦች፣ አትክልትና ፍራፍሬ አቅርቦት፣ ስርጭትና ተደራሽነት እቅድ አፈፃፀሙ ከደንበኞች ፍላጎት አንጻር መሆኑን የፋይናንስ ስራው በሲስተም በሚፈለገው ደረጃ IFRS ሂሳብ የመዝጋት አመታዊ የፋይናንስ ሪፖርትን በተሰጠ ግዜ ገደብ የማውጣት ሂደት ተከትሎ መሰራቱን እንዲሁም የሰው ሃብት ለማብቃት እና ሀብት አጠቃቀምን አሳድጎ ያለ ስራ የተቀመጡ ንብረቶችን አንቀሳቅሶ ውጤታማ ለማድረግ የተሰሩ ሥራዎች አፈፃፀም ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ ግምገማውን ሲያጠቃልሉ በአጠቃላይ በኮርፖሬሽን ደረጃ በዘርፎች፣ በዳይሬክቶሬቶች እና ጽ/ቤቶች በእቅድ አፈጻጸሞች ላይ የተደረገው ውይይት በባለቤትነት መንፈስ እና የኮርፖሬሽኑን ተልእኮ ለማሳካት እና ለህብረተሰቡ የምንሰጠውን አገልግሎት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በበጀት ዓመቱ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፣ ያልተሰሩ ስራዎች በድክመታችን አለመከናወናቸውን ተቀብለን ሁሉንም ችግር በአንዴ መፍታት ባይቻል ቅድሚያ ለሚሰጠው ጉዳይ ቅድሚያ እየሰጠን እንሰራለን ብለዋል ፡፡

001_6.jpg

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አመራርና ሠራተኞች በአራተኛውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር “የገበያ ማረጋጊያ ሥራችንን እያጠናከርን አረንጓዴ አሻራችንን እናሣርፋለን” በሚል መሪ ቃል ሆለታ በሚገኘው የኮርፖሬሽኑ የግብይት ማዕከል የችግኝ ተከላ አካሂደዋል፡፡ ከተለያዩ የኮርፖሬሽኑ የንግድ ሥራ ዘርፎች የተውጣጡ ሠራተኞችና የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ቅዳሜ ሀምሌ 23 ቀን 2014 ዓ/ም በተካሄደው መርኃ ግብር ላይ ከ1,300 በላይ የቅመማ ቅመም፣ የፍራፍሬ፣ የግቢ ውበትና የጥላ ዛፎች ተከላ የተካሄደ ሲሆን በተመሳሳይ መርኃ ግብሮችም በኮርፖሬሽኑ የተለያዩ ቅርንጫፍ ማዕከላት መሰል የተከላ መርሃ ግብሮች ተከናውነዋል፡፡

 

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ በችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ኮርፖሬሽኑ በተለይም ካለፉት አራት በተካሄዱት አረንጓዴ ዐሻራ የማኖር አገራዊ ጥሪዎች የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ክንውኖችን በስፋትና በተከታታይነት ሲያካሂድ መቆቱን አስታውሰው፤ እስካሁን በተካሄዱ የተከላ መርኃ ግብሮች ከተተሉት ችግኞች 84 በመቶው መጽደቃቸውን ገልጸዋል፡፡ በያዝነው ዓመትም ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ የቅመማ ቅመም፣ የፍራፍሬ፣ የውበትና የጥላ ዛፎችን በሆለታ የግብይት ማዕከልና በሌሎችም የኮርፖሬሽኑ ቅርጫፍ ማዕከላት በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

 

የችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ የደን ሽፋንን ለማሳደግ ብሎም አረንጓዴ ልማትን ለማረጋገጥ ከሚኖረው አስተዋጽዖ በተጨማሪ መልሰው ምርት መስጠት የሚችሉ ችግኞች የሚለሙበት በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

የአረንጓዴ ልማት እንዲሳካ እንደ አገር ሰፊ ርብርብር እየተደረገ መሆኑን ያወሱት ዋና ሰራ አስፈጻሚው፤ በተለይም ዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት እየተስተዋሉ የሚገኙ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና አፈር ለምነት እጦትን ለመከላከል የችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ከመሆኑ አኳያ ሁሉም በየአካባቢው ሥራውን በተገቢው መልኩ ለመከወን የሚያስችል በቂ ዝግጅት፣ ትግበራና ክትትል በማድረግ የበኩሉን የልማት አስተዋጽዖ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

02.jpg

 በሥራ አካባቢ ደኅንነትና ጤንነት ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት ሥልጠና ከኮርፖሬሽኑ ዋና መሥሪያ ቤትና ከንግድ ሥራ ዘርፎች ለተውጣጡና በተለያዩ መደቦች ላይ ለሚሠሩ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ከግንቦት 9-12/2014 ዓ/ም በሁለት ዙር በዋናው መሥሪያ ቤት የሥልጠና አዳራሽ እየተሰጠ ይገኛል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ በስፋት እያካሄደ የሚገኘው የአቅም ግንባታ እንቅስቃሴ አንድ አካል የሆነውና ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየተሰጠ የሚገኘው ይህ ሥልጠና በሥራ አካባቢ ደኅንነትና ጤንነት ዙሪያ የሠራተኛውን ዕውቀትና ክህሎት በማጎልበት ኮርፖሬሽኑና ሠራተኛውን ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ በመተንበይና ተመጣጣኝ የመፍትሔ አማራጮችን በማስቀመጥ ተቋሙ ዓላማዎቹንና ግቦቹን እንዲያሳካ የራሱን አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ተገልጿል፡፡

 

ሥልጠናው በዋነኝነት በመሠረታዊ የደህንነትና ጤንነት መሠረታዊ ሃሳቦች፣ በሥራ ቦታ ስጋት ግምገማና መቆጣጠሪያ ዘዴዎች፣ በሥራ አካባቢ የደኅንነት ጠንቆችና የመከላከያና መቆጣጠሪያ መንግዶች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ተሣታፊዎች በሥልጠናው ያገኙትን ክህሎትና ግንዛቤ ወደ ተግባር በመቀየር ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል፣ በሥርዓት የሚመራና በቅንጅት የሚፈጸም የልማት እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማድረግ የራሱ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አብረውት ከሚሰሩ ደንበኞችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የምክክር መድረክ ሰኔ 15/ 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል አካሄደ፡፡ በመድረኩ ላይ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በገበያ ማረጋጊያ ስራዎች በትስስር የሚሰሩ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች፣ ከፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተወከሉ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ለኮርፖሬሽኑ ምርት እና አገልግሎት አቅራቢ የመንግስት እና የግል የንግድ ተቋማት ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ፣ የዱቄት ፋብሪካ ባለንብረቶች ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩ በቀረበው የውይይት የመነሻ ጽሁፍ በኮርፖሬሽኑ ንግድ ስራ ክፍሎች እና ኮርፖሬት ሎጅስቲክስ ዳሬክቶሬት በሚሰሩ የምርትና አገልግሎት እንቅስቃሴዎች ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች እና በደንበኞችና መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚረዱ ሃሳቦች በኮርፖሬሽኑ የአሰራር ዘዴና አገልግሎት ማሻሻያ ዳ/ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ትእዛዙ ኃ/ጊዮርጊስ ቀርቧል፡፡
የመነሻ ጽሁፉን ተከትሎ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ከኮርፖሬሽኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

በውይይቱ ኮርፖሬሽኑ ለአርሶአደሩ እና ለሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ፍጆታ እቃዎች አምራቹ የገበያ እድል መፍጠሩ & ከአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት መንግስት በድጎማ ለገበያ ማረጋጊያ የሚያቀርባቸውን የምግብ ዘይት እና ስኳር የሀገር ውስጥና የውጭ ስንዴ በተመደበለት ኮታ መሰረት ለህብረተሰቡ በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በማቅረብ ገበያን ለማረጋጋት ያደረገው ጥረት በተመሳሳይ በአቅርቦት እጥረት ምክንያት የተከሰተውን የሲሚንቶ ዋጋ ውድነት ለማረጋጋት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በመሸጥ አጋርነቱን ማሳየቱ የኮርፖሬሽኑ አመራር እና ሰራተኞች ለደንበኞች የሚሰጡት መስተንግዶ ጥሩ መሆኑ በጥንካሬነት ተገልጾል፡፡

እንደ ችግር ከተነሱት ጉዳዮች መካከል በስንዴ፣ የምግብ ዘይትና ስኳር የአቅርቦት መዘግየት መታየት፣ የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረት፣ የፍጆታ ምርቶች ግብይት ላይ አስገዳጅ ምርቶችን ውሰዱ መባል የሚሉትን ጉዳዮችን ኮርፖሬሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲፈለግ ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡

ለተነሱት አስተየየቶች የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ደንበኞቹና ባለድርሻ አካላት በሚጠብቁበት ደረጃ አገልግሎቱን ለመስጠት እና ባቀደው ዕቅድ ልክ አፈጻጸሙን ለማሳካት በሀገር ውስጥ በሚፈለገው መጠንና ዋጋ የእህል ምርት ገበያው ላይ አለመገኘት፣ በመንግሥት ድጎማ ለገበያ ማረጋጊያ ከውጭ ሀገር የሚገዛውና በኮርፖሬሽኑ የሚሰራጨው የውጭ ስንዴ ግዥ ጨረታ መስተጓጎል፣ ለገበያ ማረጋጊያ ከውጭ ለሚገዙ የፍጆታ ሸቀጥ ምርቶችም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ፍላጎትና አቅርቦቱ አለመመጣጠን፣ ኮርፖሬሽኑ ለውጭ ገበያ የሚያቀርባቸው የቡና፣ የቅባት እህልና ጥራጥሬ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የገበያ ዋጋ መብለጥና የምርቶቹ ዋጋ መዋዠቅ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸው በውይይቱ ወቅት ተብራርቷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የመንግስት የልማት ድርጅት እንደመሆኑ ወጪውን ራሱ እንደሚሸፍንና የትርፍ ህዳጉ ግን እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ተመላከቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ በውይይቱ ማጠቃለያ በመድረኩ የተሳተፉ አካላትን በማመስገን የተሰጡ አስተያየቶችን እንደ ግብአት ወስደን አገልግሎታችንን ይበልጥ ለማሻሻል እንጠቀምበታለን ብለዋል፡፡ መድረኩ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም የላቀ አጋርነት ላሳዩ ደንበኞች የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር የተካሄደ ሲሆን 13 ደንበኞች የእውቅና የምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት ከኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ እጅ ተበርክቶላቸዋል፡፡

Kaizen01.jpg

በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤትና በአራቱም ዘርፎች የካይዘን እጩ አማካሪዎች የትግበራ ግምገማ ግንቦት 9/2014 ዓ.ም ተካሄደ፡፡ የግምገማ መድረኩን የመሩት አቶ ትእዛዙ ኃ/ ጊዮርጊስ የኮርፖሬት አሰራር ዘዴና የአገልግሎት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና አቶ አወል ካሳው በካይዘን ኢንስቲቲዩት የሎጀስቲክስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡

የካይዘን ትግበራ በአራቱም ዘርፎችና በዋና መ/ቤት ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች (ፎካል ፐርሰንስ) ገለጻ አድርገዋል፡፡ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ስራ ዘርፍ ከካይዘን ትግበራ ጋር በተያያዘ ሁለት ፕሮጀክቶችን (የብልሽት ቅነሳ ስትራቴጂ እና የስራ አካባቢን ምቹ ማድረግ) እየተገበሩ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ለብልሽት ቅነሳ የሚሆኑ መፍትሄዎችን በመለየት ወደ ስራ መግባታቸውን የካይዘን ተጠሪ (ፎካል ፐርሰን) የሆኑት አቶ ዘካሪያስ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም በስራ ግቢ ውስጥ ወድቀው የተገኙ የተለያዩ ማቴሪያሎች ወደ አንድ ቦታ በማከማቸት የተገኘውን ክፍት ቦታ መጋዘን እንዲሰራበት መደረጉን እንዲሁም ንብረት በማስወገድ 900ሺ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በእህልና ቡና ንግድ ስራ ዘርፍ በተመሳሳይ የካይዘን ትግበራው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ለእህል ማደራጃና ማከማቻ ሰራተኞች ስልጠና መሰጠቱ ተጠቁሟል፡፡ ንብረት በማስወገድ ገቢ ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡ በዋና መ/ቤት ደግሞ ከማዕድን ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የልምድ ልውውጥ መደረጉና ጠቃሚ ተሞክሮዎች መገኘታቸውና መቀመራቸው ተጠቅሷል፡፡ በተመሳሳይ በሌሎችም ዘርፎች ከካይዘን ትግበራ አኳያ የተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ገቢዎች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

አመራሩ የካይዘን ትግበራን ለመተግበርና ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑ እና ካይዘንን ለመተግበር ምንም ኣይነት የበጀት ችግር አለመኖሩ በጥንካሬ፤ ወጥ የግንኙነትና የውይይት ጊዜ አለመኖር እና በሙሉ አቅም አለመስራት እንደ ክፍተት ከተነሱት ዋንኞቹ ናቸው፡፡ በተነሱ ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡ በተለይም የድጋፍና ክትትል አግባቡ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተመልክቷል፡፡