የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአገራችን ያለውን መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ ምርቶች አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረትን ለመቋቋም የተለያዩ የፍጆታ ምርቶችን በማከፋፈል ገበያውን ማረጋጋት አንዱ አገራዊ ተልዕኮው ነው፡፡

ዘንድሮም ኮርፖሬሽኑ ከውጭ የገዛውን ለአገር ውስጥ የገበያ ማረጋጊያ የሚውል ስንዴ በዕቅድ ከተያዘው 8 ሚሊየን ኩንታል ውስጥ የመጀመሪው ዙር አገር ውስጥ በማስገባት ወደ ተለያዩ ክልሎች በማሠራጨት ላይ ይገኛል፡፡

በመጀመሪው ዙር አራት ሚሊየን ኩንታል ስንዴ በአዲስ አበባ እና ከክልሎች በድሬደዋ፣ በባህር ዳር߹ በሻሸመኔ እና በአዳማ በተዘጋጁ የማሰራጫ ማእከላት እየገባ ነው፡፡

የስንዴ ግዥው በ11 ቢሊየን ብር የተከናወነ ሲሆን ስርጭቱ በአገራችን በሁሉም ክልሎች የኢትዮጵያ የንግድ እና ቀጠና ትስስር ሚኒስቴር በሚሰጠው የኮታ መጠን መሰረት በዋነኝነት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለሚገኙ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆን ለሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት፣ ለአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለፖሊስ ሠራዊት፣ ለማረሚያ ቤቶች፣ ዳቦ አምርተው ለኅበረተሰቡ ለሚያቀርቡ ድርጅቶችና ለሌሎችም አቅርቦቱ ለተፈቀደላቸው አካላት የሚሠራጭ ሲሆን የአቅርቦቱ መኖር የስንዴ ገበያ ዋጋ እንዳይንር አስተዋጽዖኦው የጎላ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሚያካሂዳቸውን የንግድ ሥራዎች በተሻሻሉ የአሠራር ዘዴዎች በመደገፍና ዘመናዊ፣ ወጪ ቆጣቢና የተቀላጠፈ አሠራርን ሥራ ላይ ለማዋል የሚረዱ የተለያዩ ዕቅዶችንና የአሠራር ስልቶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል ቀደም ሲል በመመሪያ ላልተደገፉ የተለያዩ የተቋሙ አሠራሮች መመሪያዎችን በማዘጋጀትና የነበሩትንም በማሻሻል የአገልግሎት አሠጣጥንና የስትራቴጂያዊ ግቦችን ስኬታማነት ማረጋገጥ ይገኙበታል፡፡ በዚህም ረገድ በተዘጋጁ ረቂቅ መመሪያዎች ዙሪያ የኮርፖሬሽኑን የበላይ አመራርና የሥራ ኃላፊዎች ያሣተፈ ውይይት ነሀሴ 12 ቀን 2013 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ውይይት ከተካሄደባቸው ረቂቅ መመሪዎች መካከል የዕውቅናና ሽልማት አሰጣጥ፣ የተሸከርካሪ ስምሪት እንዲሁም የሥልጠናና ትምህርት መመሪያዎች የሚገኙበት ሲሆን ከተሣታፊዎች ጋር በተካሄዱ ውይይቶች የተገኙ ግብዓቶችን በመቀመር በቅርቡ ጸድቀው በኮርፖሬሽን ደረጃ ተግባራዊ እንደሚደረጉ በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2013 ዕቅድ አፈጻጸምና በ2013 የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ከሁሉም የንግድ ዘርፎችና ከኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት ሠራተኞች ጋር አጠቃላይ ውይይቶች አካሂዷል፡፡ ውይይቶቹ በኢንሥኮ የበላይ አመራሮች ሰብሳቢነት የተካሄደ ሲሆን የተሳታፊዎቸን ለኮቪድ-19 ተጋላጭነት ለመቀነስ በሚያስችል መልኩ በዙር ጎተራ በሚገኘው ኮርፖሬሽኑ የስብሰባ አዳራሽ ነሀሴ 21፣ 22፣ 25፣ 26 እና 28 ቀን 2012 ዓ/ም ተካሂደዋል፡፡

የኢንሥኮን የ2012 ዓ/ም የንግድ ሥራዎች የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት ላይ ሽፋን ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የተቋሙ የ2012 ዓ/ም የግዢና አፈፃፀም የሽያጭ አፈፃፀም፣ ገበያን ከማረጋጋት አንፃር የተከናወኑ ዓበይት ተግባራት የሚገኙበት ሲሆን የሰው ሀብት ሥራ አመራርና ልማት፣ የፋይናንስ ሀብት አጠቃቀም፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽን፣ የሪፎርምና የመልካም አስተዳደርና ሌሎችም ተቋማዊ ዕቅዶች አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የግዢ ዕቅድ አፈጻጸምን በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ 10.3 ሚሊዮን ኩንታል እህል፣ ቡና፣ የፍጆታ ዕቃዎች እና አትክልትና ፍራፍሬ በብር 11.3 ቢሊዮን ለመግዛት አቅዶ 7.9 ሚሊዮን ኩንታል በብር 8.7 ቢሊዮን በመግዛት የዕቅዱን በመጠንም ሆነ በዋጋ 77 በመቶ ማከናወኑ ተገልጿል፡፡

የሽያጭ አፈፃፀምን በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ በ2012 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥና በውጪ ገበያ ብር 8.9 ቢሊዮን ዋጋ ያለው 10.1 ሚሊዮን ኩንታል እህል፣ ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የፍጆታ ዕቃዎች እንዲሁም የግዢና ማማከር አገልግሎት ለመሸጥ አቅዶ ብር 5.9 ቢሊዮን ዋጋ ያለው 7.0 ሚሊዮን ኩንታል ምርትና አገልግሎት በመሸጥ ዕቅዱን በመጠን 70 በመቶ በዋጋ ደግሞ 67 በመቶ ማከናወኑ ተጠቅሷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ሲሚንቶ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያሰራጭ በመንግሥት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከፋብሪካዎች በመረከብ በሥርጭት እንዲሸፍናቸው በተሰጡት አካባቢዎች የ25.8 ብር ሚሊዮን ዋጋ ያለው 83.6 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ ጠቅላላ ሽያጭ አከናውኗል፡፡

በግዢና ሽያጭ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ ካሳደሩ ምክንያቶች መካከል የመግዣ ካፒታል እጥረት፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ምርትን የማስተዋወቅና ገበያ የማፈላለግ ሥራ በበቂ ሁኔታ አለመሠራቱ፣ እሴት ጨምሮ መሸጥ ላይ ትኩረት አለመደረጉ፤ የውጭ ደንበኞች የሚሠጡት ዋጋ በተለይም የቡና፣ ቅባት እህልና ጥራጥሬ ዋጋ ወጪን ሸፍኖ ለመሸጥ የማያስችል ዝቅተኛ ዋጋ መሆን፤ የግል ላኪዎች በኤክስፖርት የሚደርስባቸው ኪሣራ በሚያስገቡት ሸቀጥ ስለሚያካክሱት ዋጋ ሰብረው መሸጣቸውና በሚፈለገው መጠን ለሽያጭ መደብሮች የሸቀጥ አቅርቦት ማቅረብ አለመቻሉ፤ ከባንክ ኦቨር ድራፍት /ብድር/ በመግባት እንዲፈታ እየተደረገ ቢሆንም ብድሩ ከፍተኛ የወለድ ወጭ ያለው መሆኑ፣ የሀገር ውስጥ ስንዴ መግዣ ዋጋ በእጅጉ መጨመር፤ በኮሮና ፋይረስ ወረርሽን ምክንያት የእህል አቅርቦት መቀነስና የዋጋ መጨመር፤ የሚሉት ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች ይገኙበታል፡፡

የአመራሩን ሁኔታ በተመለከተም አመራሩ የተሰጠውን ተግባር በቅንነት ተቀብሎ ለመፈፀም ጥረት የሚያደርግ መሆኑ፤ የነበረውን የአመራር ክፍተት ሸፍኖ በመስራት በኩል የነበረው እንቅስቃሴ በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ የነበሩትን ችግሮች ለይቶ የተሸሻሉ አሰራሮቸን ሥራ ላይ በማዋል የተቀናጀ እንቅስቃሴ መደረጉ አንዲሁም ኮርፖሬሽኑን ትርፋማና ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት አበረታች መሆኑ በጥንካሬ የተመላከተ ሲሆን በየዘርፉ የተበተነ አሠራር መኖሩ፤ ተቋሙ እንደ ኮርፖሬሽን የተደራጀና የተጠቃለለ ሆኖ አለመመራቱ፤ ከቀመጡ የአሠራር መመሪያዎች ውጭ የሚፈፀሙ ተግባሮች መኖራቸው በድክመትነት ተገምግመዋል፡፡

በቀጣይ እንደ ተቋም አፈጻጸምን ለማሳደግ በትኩረት አቅጣጫነት ከተቀመጡ ጉዳዮች መካከልም አፈጻጸሞች አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ጉድለትና ድክመት የታየባቸውን በማሻሻል ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር አልሞ መስራት፣ ውጤታማ የሀብትና ንብረት አጠቃቀምን ተግባራዊ ማድረግ፣ የተለያዩ የገበያ መረጃዎችን በጥራትና በስፋት ከአምራቹ፣ ከአቅራቢው፣ ከተጠቃሚው በማሰባበስብ ሥራ ላይ ማዋል፤ በወጪ ንግድ ያላሰለሰ ጥረትና ድጋፍ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሣደግ እንዲሁም ልዩ ልዩ አጋዥ ሪፎርሞችን ሥራ ላይ ማዋልና የደንበኞችንና ባለድርሻ አካላትና ተጠቃሚዎችን እርካታ ማሣደግ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የጋራ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡

በኮርፖሬሽን ደረጃ ወጥነት ያለው የመረጃ አደረጃጀትና ሥርጭትን በመጠቀም ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የውስጥ መረጃ ልውውጦችንም ቀልጣፋና የተሟላ ለማድረግ በሚቻልበት አሠራር ላይ ያተኮረ ሥልጠና ነሀሴ 18 ቀን 2012 ዓ/ም በኮርፖሬሽኑ የስብሰባ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ በተሰጠው ሥልጠና የኮርፖሬሽኑ ም/ዋና የሥራ አስፈጻሚዎች፣ የዘርፍ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ከፍተኛና መካከለኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የጽሕፈት ሥራና የቢሮ ውበት አስተዳደር ባለሙያዎች እንዲሁም የሪከርድና ማህደር ባለሙያዎች ተሣትፈዋል፡፡

ዓላማው የመረጃ አያያዝና አሰረጫጨትን በካይዘን ፍልስፍና በመታገዝ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት ፣በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመታገዝ የደብዳቤዎች ምልልስን በማስቀረት ግዜን እና ጉልበትን ከብክነት ማዳን የሚያስችሉ አሰራሮችን ማመላከት በሆነው ስልጠና መነሻነት የተለያዩ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡

በሥልጠናው ማጠቃለያ በኮርፖሬሽን ደረጃ ወጥ የሆነ መረጃ አደረጃጀት እንዲኖር በሙያው የሚመለከታቸውን ባለሙያዎች ያቀፈ የመመሪያ ዝግጅት ኮሚቴ እንዲዋቀር ቀደም ብሎ ለመረጃ አያያዝ በግብዓትነት የተጠየቁ በተቻለ አቅም ግዥ እየተፈጸም እንዲቀርብ በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጥ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

COVID 19 Fight

 

በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተከሰተውና በፈጣን ሁኔታ በሁሉም አህጉራት እተሰራጨ የሚገኘው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽን ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት በመከላከል ከፍተኛ እንቅሳቀሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሠራተኛውን ደህንነት በመጠበቅ ለህብረተሰቡ የሚሰጠው አግልጎሎት ሳይቋረጥ ለመቀጠል እንዲቻል የድርጊት መርሃ ግብር አዘጋጅቶ የተለያዩ እንስቃሴዎች ማናወን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ የበሽታው ስርጭት በሠራተኛ ጤንነት፣ በኮርፖሬሽኑ ግብይት እና ገቢ ላይ ተፅዕኖ በመተንበይና ይህንንም ተፅዕኖ የሚያሳድር ከመሆኑ አኳያ የድርጊት መርኃ ግብሩ በእነዚህ ላይ ትንተና በማካሄድ ችግሩን መቋቋም የሚቻልበት አሠራር ነድፎ ወደ ትግበራ ጀምሯል፡፡

 

የኮቪድ-19 ሥርጭትን የመከላከሉ መርኃ ግብር በሽታው በኮርፖሬሽኑ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ትንታኔ መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ሠራተኞች ከሥራቸው ባህሪ አንጻር በተለይም ከደንበኞች መስተንግዶ ጋር በተያያዘ ተጋላጭ መሆናቸው፤ ሠራተኞች በጋራ የሚጠቀሙባቸው የመገልገያ መሣሪያዎች መኖራቸው፤ ሠራተኞች በተበታተነና በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ መሆኑ የተጋላጭነት ስጋትን የሚጨምር መሆኑ እንዲሁም ከአጠቃላይ ከቫይረሱ ስርጭት መስፋፋት ጋር በተያያዘ ሠራተኛው ለበሽታው እጋለጣለሁ በሚል የስነ ልቦና ጫና የሚያድርበት መሆኑ ለመከላከል ሥራዎች መነሻ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡

 

የኮርፖሬሽኑን ዓበይት የንግድ ተግባራት ጋር በተያያዘም ከታዳጊ አገሮች ከፍትኛ ምርት የሚያስገቡ እንደ ቻይና፣ አውሮፓና አሜሪካና ሌሎችም ያሉ አገራትና አህጉራት የንግድ እንስቃሴቸው በመገደቡ የተነሳ ከውጭ የሚያስገቡት ምርት ፍላጎት አብሮ በመቀዝቀዙ ኢትዮጵያ ጨምሮ ሌሎች ታዳጊ አገራት ወደ ውጭ ይልኩት የነበረው ምርት በመጠንም ሆነ በዋጋ መቀነሱ በችግርነት ተጠቅሷል፡፡ የበሽታው ሥርጭት በአጭር ጊዜ የቀንሳል ተብሎ ስለማይጠበቅ ኮርፖሬሽኑ የገጠመውን ኤክስፖርት መቀዛቀዝ እሰከ ሚቀጥለው በጀት ዓመት አጋማሽ እንደሚቀጥል መገመቱ በስጋትነት ተቀምጧል፡፡

 

የቫይረሱን ወረረርሽ ለመከላል በሚሰጠው ቅድሚያ ትኩረትና በሌሎች ምክንያቶች የውጭ ምንዛሪ ዕጥረቱ ችግር ባለመቀረፉ በኮርፖሬሽኑ የውጭ ምርቶችን በማስገባት ሂደት ላይ ተትዕኖው ሊበረታ እንደሚችል የገመተ ከሞኑ ባሻገር የኤክስፖርት ገበያ መቀዛቀዝ እና በሀገር ውስጥ የእርዳታ ድርጅቶች (እንደ ዓለም ምግብ ፐሮግራም እና አደጋ ስጋትና ዝግጁነት ኮሚሽን ዓይነት) የእህል ዋጋ በመጨመሩ የተነሳ በሀገር ውስጥ የሚገዙት የነበረ መጠን መቀንስ የተነሳ የኮርፖሬሽኑ እህል ሽያጭ በተለይም ከፍተኛ ድርሻ ያለው በቆሎ ሽያጭ ቀንሶ መታየቱና ይህም በተራው የኮርፖሬሽኑ የትርፍ መጠን ይቀንሰቀዋል ተብሎ መጠበቁ በንግድ ሥራ ተጽዕኖነት ተቀምጠዋል፡፡

 

እነዚህን ችግሮች ለመፍተታት ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ የበሽታውን ሥርጭት የመቋቋሚያ ትግበራዎች ነድፎ ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህም በተዋርድ ኮሚቴ በማቋቋም ስለወረርሽኙና የመከለከያ ዘዴው ሠራተኛው የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረው የተለያዩ የተግባቦት ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን በሥራ ገበታ የሚኖረው ሠራተኛ በተቻላ ቦታ ለመቀነስ እንዲቻል የተጠራቀመ የአመት ፈቃድ ያላቸው ሠራተኞች ፈቃዳቸውን እንዲወስዱ ወይም በቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ ማድረግ ተችሏል፡፡ የጤና ችግር ያለባቸው ሠራተኞች በተቻለ መጠን ዕረፍት እንዲወስዱ ማድረግ፣ በቅብብሎሽና በቅርርብ የሚሰሩ ሥራዎች አካባቢ ሠራተኞች ርቀታቸውን እንዲጠብቁና በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር ማድረግ፤ የጋራ መጠቀሚያ መሳሪያዎችን ፅዳታቸውን የጠበቁ እንዲሆን ማድረግ፤ ሠራተኞች ወደ ስራ ሲገቡ እና ወደ ክሊኒክ ለህክምና ሲሄዱ በሙቀት መለኪያ መሳሪያ ሙቀታቸውን እንዲለኩ ማድረግ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ሠራተኞች እንዲጠቀሙ በማድረግ በሽታውን የመከላከል ጥረቶች ተደርገዋል፡፡

 

በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የኮርፖሬሽኑ ይዞታዎች የበለጠ ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው የተባሉ የሥራ ቦታዎች ተለይተው ሥራ አመራሩን ያካተተ ተደረጎ በግብረመልስ ላይ የተመሠረቱ ርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ የሰራኞች ሰርቪስ እጥረትን ለመፍታት ከሎጂስቲክ ጋር በመመካከር ተጨማሪ መኪኖች እንዲመደቡ ተደርጓል፡፡ የንጽህና መጠበቂያ ሰኒታይዘሮችን፣ አልኮልና ፈሳሽ ሳሙና ለሰራተኞች እንዲከፋፈል የተደረገና ሲሆን ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆኑ የእጅ መታጠቢያዎች እንዲጠቀሙም ተደርጓል፡፡

 

ከግብይት ሥራዎች ጋር ተያይዞ በኤክስፖርት ገበያ እየገጠመ ያለውን የገበያ መቀዛቀዝ ለመቋቋም በዝቅተኛ ትርፍ ወይንም ወጪን ብቻ በሚሸፍን መልኩ ዋጋ በመስጠት ለማበረታታት ጥረት በማድረግ፣ ከከፍተኛ ምርት አምራቾች ወይም ኢንቨስተሮች ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ምርታቸው ለኮርፖሬሽኑ የሚያቀርቡበት መንገድ በቀጥታ በመደራደር እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ እጥረት እየገጠመ ያለውን መሠረታዊ ሸቀጥ በበቂ ሁኔታ ለህብረተሰቡ ያለማቅረብ ችግር ለመቅረፍ ኮርፖሬሽኑ ከኤክስፖርት የሚያገኘውን ገቢ በተቻለ መጠን ከውጭ ሸቀጥ የሚያስገባበትን ሁኔታ ከባንኮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቋቋም እየተሠራ ይገኛል፡፡

 

በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ ሊደርሰው የሚችለው የንግድ ኪሣራ ለመቋቋም በተቻለ መጠን ሌሎች የገቢ ማስገኛ ስልቶች ላይ ጠንክሮ መሥራት እንደሚኖርበትና የበቆሎ እና ሌሎች እህሎች ሽያጭ እንደተጠበቀው ባለመሆኑ በአሁኑ ወቅት ፍላጎታቸውን እየጨመረ የመጣውን የኢንዱስትሪ ሸቀጦችና እንደዚሁም አትክልትና ፍራፍሬ ሽያጭ ላይ በርትቶ በመሥራት የሽያጭ ሥራዎችን አጎልብቶ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ በተቋም ደረጃ የጋራ ግናዛቤ የተወሰደበት ጉዳይ ሆኗል፡፡