የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና የኢፌዴሪ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ በየዘርፈቸው ለሚያከናውኗቸውና የየተቋማቱን የሥራ አፈጻጸም ለማገልበት የሚረዱ መልካም ተሞክሮዎችንና ከምርትና ገበያ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለመለዋወጥ የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ/ም በኢንሥኮ ዋና መሥሪያ ቤት ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ ተቋማቱ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን የግብይት ዋጋዎችን እንዲሁም በመረጃዎች ላይ ተመሥርተው የተሚካሄዱ ጥናትና ጥናቶችንና ትንታኔዎችን ውጤቶች በመለዋወጥ በግብርናው ዘርፍ የሚሰሩ አካላትንና የአምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ መሆኑ በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በዋነኝነት የአነስተኛ አርሶ አደሮችን የማምረት አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ድጋፎችን የማድረግ፣ በመረጃ ትንተና እና ጂአይኤስ ዙሪያ መልካ ተሞክሮዎች ከግብርና ትራንስፎርሜሽን የማግኘት እንዲሁም ከኤጀንሲው ጋር በመሆን የግብርና መረጃጃ አያያዝን የማዘመን ሥራዎችን ማከናወን የሚችልበት ዕድል እንደሚፈጥርለት ተገልጿል፡፡

በተመሣሣይም የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ በመረጃ በመረጃ ላይ የተመሠረቱ ውጤቶችን ለማግኘት የሚያስችሉ ወቅታዊ የመረጃ ግብዓቶችንና በኢንሥኮ የተተገበሩ የመረጃ አያያዝ መልካም ተሞክሮዎችን የሚያገኝባቸውን ስልቶች መተግበር የስምምነቱ አካል መሆናቸው ታውቋል፡፡

አነስተኛ አርሶ አደሮችም በወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎች ላይ ተመስርተው ከሚነደፉ ስትራቴጂዎች፣ ፖሊሲዎችና ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ እንደሚሆን በስምምነቱ ሰነዱ ተመልክቷል፡፡

Planting01.jpg

ደን ህይወት ነው፡፡ አዎ በእርግጥም ደን ህይወት ነው፡፡ ዓለማችንን እያስጨነቀ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤው የደን መመናመን ነው፡፡ ምድራችን ያለደን ውበት የላትም፡፡ ደን ስትለብስ ግን ግርማ ሞገሷን ትላበሳለች፤ እስትንፋሷም ይስተካከላል፡፡

 

ዕጽዋት የከተማችንን የአየር ንብረት ለመጠበቅም ሆነ አካባቢን ለማስዋብ ያላቸው ጠቀሜታ የጎላ ከመሆኑ አንጻር ችግኞችን መትከል የተተከሉትን ተንከባክቦ ማሳደግ ለአካባቢ ጥበቃ መሠረት ነው፡፡ በያዝነው በጀት አመት አረንጓዴ አሻራ እናሳርፍ፤ በአንድ ጀምበር 200 ሚሊየን ችግኝ እንትከል!” በሚል መሪ ቃል በመላ ሀገሪቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ መርኃ ግብሩ በዋናነት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ/ም የሚከናወን ሲሆን እንቅስቃሴው ቀድሞ ተጀምሯል፡፡ ይህ መርኃ ግብር የሀገሪቱን የደን ሽፋን ትርጉም ባለው መልኩ አንድ እርምጃ ወደ ፊት የሚያራምድ መሆኑ በብዙዎች ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

 

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ይህንን ሀገራዊ አጀንዳ ተቀብለው ሀምሌ 6 ቀን 2011 ዓ/ም ሳሪስ በሚገኘው የኮርፖሬሽኑ የእህል ማከማቻ ቅጥር ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሂደዋል፡፡

 

በችግኝ ተከላው ወቅት የኮርፖሬሽኑ ኮርፖሬት ሰርቪስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታሪኩ በራሱ መርሃ ግብሩን አስመልክተው ደን ከሰው ልጆች ህይወት ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለውና ከደማችን ጋር የተያያዘ መሆኑን በመጥቀስ ንጹህና ያልተራቆተ አካባቢን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ያሳሰቡ ሲሆን ችግኞችን መትክል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትም እንዲጸድቁ ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ በመጠቆም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ በአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሙ የችግኝ ተከላን በዋና መሥሪያ ቤቱና በክልል የግብይት ማዕከላት የነደፈ ሲሆን የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የአካባቢ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡

 

ዘንድሮም የተሣተፉት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በዕለቱ የተተከሉትን ችግኞችም ሆነ የቀደሙትን ተንከባክበው ለፍሬ እንደሚያበቁ በችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ላይ ቃል ገብተዋል፡፡

addis.jpg
አዲስ አበባችን ለረጅም አመታት በመዝናኛ ቦታዎች እጥረት ነዋሪዎቿ ሲወቅሷት ኖረዋል:: ከተሞች የቱንም ያህል በመሰረተ ልማት ቢለሙም በወንዝ ዳርቻዎች የሚካሄድ ልማት ከሚሰጠው የአእምሮ እርካታ አንጻር እምብዛም ነው፡፡ በእኛም ሀገር ሁኔታ በወንዞችና ሀይቆች ዙሪያ የተመሰረቱ ከተሞች ምን ያክል ነዋሪዎቻቸውን አለፍ ሲልም ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ጎብኝዎችን አእምሮ እንደሚያዝናኑ ግልጽ ነው፡፡ መዲናችን አዲስ አበባ ጸጋው እያላት ጸጋዋን ሳታለማና ሳትጠቀምበት ለረጅም ግዜ ቆይታለች፡፡ አሁን ግን ለረጅም ጊዜ የቆሻሻ መጣያ ሆነው የከረሙ ወንዞቿን ለማልማት ቆርጣ ተነስታለች፡፡
ከእንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ ከተማዋን ለሁለት ከፍለው በሚፈሱ ወንዞች ግራና ቀኝ የሚሰራው የወንዝ ዳርቻ ልማት የተግባር እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ልማቱ 51 ኪ/ሜ ርዝመት የሚሸፍን ሲሆን በ29 ቢሊዮን ብር ወጭ ይከናወናል፡፡ የወንዝ ዳርቻው ልማት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠሩም በላይ ከተማዋን ጽዱና ማራኪ በማድረግ በኩል ድርሻው የጎላ ነው፡፡ የወንዝ  ዳርቻ ልማቱ ሲጠናቀቅ መዲናችንን እንደ ስሟ አዲስ አበባ ውብ እና ማራኪ በማድረግ የቱሪዝም መስኩን የበለጠ በማነቃቃት በኩል ልዩ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በሳምንቱ መጨረሻ በስራ ደክሞ የሰነበተ አእምሯቸውን ዘና ለማድረግ ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚጓዙ የከተማዋ ነዋሪዎች መልካም አጋጣሚ ይሆንላቸዋል፡፡ በዚህም ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን እንዲሁም ድካማቸውን መቀነስ ያስችላቸዋል፡፡  ከዚህም በተጨማሪ በየእለቱ በትርፍ ሰዓታቸው መዝናናት ለሚፈልጉ የመዲናዋ ነዋሪዎች እንደ መዝናኛ አማራጭ ከመሆኑም ባሻገር ከተማዋን ጽዱና ማራኪ በማድረግ በኩል ድርሻው የጎላ ነው፡፡ 
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሚያደርጋቸው ተሳትፎዎች የዳበረ ልምድ ባለቤት ነው፡፡ በማህበራዊ ጉዳዮች በመሳተፍና ድጋፍ በማድረግ በጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ግንባር ቀደም ተሳትፎ ያለው ኮርፖሬሽኑ በ “ሸገርን ማስዋብ” እቅድ ላይም ያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ የወንዝ ዳርቻ ልማት ከግብ እንዲደርስ ባለድርሻ አካላት ርብርብ በማድረግ ላይ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን 250¸000 ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገባ ሲሆን በቀጣይም አጋርነቱን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኑ ታውቋል፡፡ በእርግጥም ሸገርን ማስዋብ ትኩረት ሊነፈገው የማይገባው ጉዳይ መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡
Algeria01 01.jpg
 
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአልጄሪያ በተካሄደው 52ኛው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ ተሣትፏል፡፡ ከሰኔ 15-20/2011 ዓ/ም በአልጄሪያ ዋና ከተማ አልጀርስ በተካሄደው በዚሁ የንግድ ዓውደ ርዕይ ላይ የኮርፖሬሽኑ የእህልና ቡና ንግድ ሥራ ዘርፍ በአዲስ አበባ የንግድ ምክር ቤት አስተባባሪነት ከሦስት የግል ቡና አምራች ድርጅቶች እንዲሁም ቆዳ አምራቾች ጋር በመሆን የመጀመሪያውን ተሣትፎ አድርጓል፡፡ በትርዒቱ ላይ የኢትዮጵያን የቡና መገኛነት፣ አገሪቱ የምትታወቅበትን የኮፊ አራቢካ የቡና ዙርያ ተመራጭነትና ባህሪ ለተሣታፊዎች ማስተዋወቅ የተቻለ ሲሆን፤ አገሪቱ በዓለም ዓቀፉ የቡና ምርት ግብይት ውስጥ የሚኖራትና ተሣትፎና ድርሻ በተለይም የደንበኞችን ቁጥር ለመጨመርና የኮርፖሬሽኑን ምርቶች ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ ግንኙነቶችና ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ 
 
አልጄሪያ በዓለም ላይ ቡና ተጠቃሚ ከሆኑ አገሮች አንዷ ሰትሆን በያዝነው የፈረንጆች ዓመት 76 ሺህ ሜትሪክ ቶን ቡና ከውጭ አስገብታለች፡፡ ይሁን እንጂ በዓለም ላይ በጣዕሙም ሆነ በጥራቱ ተመራጭ የሆነ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የምትታወቀው አገራችን ከዚህ ገቢ ምርት ውስጥ የነበራት ድርሻ 19 ሜትሪክ ቶን ወይም ከ1 በመቶ ያነሰ ሆኖ መገኘቱ በቡና ወጪ ንግድ ላይ ድርሻን ተሣትፎን እጅጉን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አመላክቷል፡፡
 
በአሁኑ ወቅት በቡና ወጪ ንግድ ዘርፍ የሚታዩ ተግዳሮቶች እየጠነከሩ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ቀስ በቀስ ከገበያ የመውጣት ስጋቶችን ከወዲሁ ማስቀረት ከመቻል አኳያ በንግድ ትርዒቱ ላይ ከተደረገው ተሣትፎ የተወሰዱ ግንዛቤዎች አዎንታዊ ሚና እንደነበራቸው ተገልጿል፡፡ 
 
አልጄሪያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ድጋፍ ሰጪነት በተዘጋጀ መድረክ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት በተለይም ከቡና አስመጪዎችና ኢንቬስተሮች ጋር መገናኘትና በተለያዩ የንግድ ማሻሻያ ጉዳዮች ላይ ገንቢ ውይይት ማድረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡ ለአብነትም በአልጄሪያ የብራዚል አምባሳደርን ጨምሮ ከሌሎች አገሪቱን ወክለው በንግድ ትርዒቱ ላይ የተገኙ ተሣታፊዎች የአገራችን የቡና ምርት የጎበኙ ሲሆን በተመሳሳይም ኢትዮጵያን ወክለው የተሣተፉ ባለሙያዎች የብራዚል ምርቶችን በመጎብኘት ጠቃሚ ግንዛቤዎችን መወሰድ ችለዋል፡፡ 
 
 
ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ማቅረብ የምትችለው ቡና በጥራቱ ከፍተኛና ተፈላጊ ሆኖ ሳለ ሌሎች አምራች አገራት ከዚህ ያነሰ ጥራት ያለው ምርት ይዘው የተሻለ ገበያ ማግኘት መቻላቸው አገሪቱ በንግዱ ዘርፍ ልትፈታቸው የሚገቡ ጉልህ ክፍተቶች መኖራቸውን ከዓውደ ርዕዩ  ተሣትፎ መረዳት ተችሏል፡፡ በተለይም በአገር ውስጥ የሚቀርበው የቡና ምርት የመግዣ ዋጋ ከዓለም የገበያ ዋጋ በእጥፍ ከሚልቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኤክስፖርተሮች ከዓለም ገበያ ውጭ መሆናቸው፤ የቡና ምርት ከአገር ውስጥ ገበያ ከተገዛበት በታች በሆነ ዋጋ ሲሸጥ በሚመለከተው አካል እርምጃ አለመወሰዱ ወይም የወጪ ንግድ የዋጋ ወለል መሰን አለመቻሉ በዓለም አቀፉ ገበያ ላይ በሚፈለገው ልክ ተወዳዳሪ ሆኖ ላለመውጣት ምክንያት መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ 
 
በአልጄሪያ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት ከአልጀሪያ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ጋር በመተባበር ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ጠቃሚ የB to B የንግድ ውይይት በጥልቀትና በተናጥል በማድረግ በቀጣይ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የሥራ ግንኙነት ለመጀመር ከሚችሉ ደንበኞች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት ንግድ ትርዒቱ ላይ ለመሳተፍ ከመጡ የብራዚል ኤክስፖርተሮች ጋር በአምባሳደራቸው በኩል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ተችሏል፡፡ 
 
በሌላ በኩል ጥራጥሬ ፣ ቅባት እህል፣ ቅመማ ቅመም እና ቡና ኢምፖርት ለማድረግ የሚፈልጉ አስመጪዎች ፍላጎታቸውን የገለፁ ሲሆን፤ ነገር ግን የአገሪቱ የአቅርቦት ዋጋ ከፍ ያለ በመሆኑ በወቅቱ ካለው ዓለም አቀፍ ዋጋ አንፃር እጅግ ውድና አዋጪ አለመሆኑን በመግለፅ ስምምነት ላይ ለመድረስና ውል ለመዋዋል ሳይቻል ቢቀርም ቀጣይ ግንኙነቶችን በማድረግ የንግድ ግንኙነቶችን ለማሳካት ጥረት የሚደረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
እነዚህ ችግሮች መፈታት ከቻሉ ኮርፖሬሽኑ የንግድ ዘርፉን ለማጎልበት ካለው አቅም ጋር ተዳምሮ በቀጣይ የቡና ምርት ግብይትን ማጎልበት የሚቻል መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በተለይም የቡና ምርትን በፍሬ ደረጃ ለገበያ ከማቅረብ ባሻገር የአገሪቱን የተለያዩ የቡና ዝርያዎች የዓለም አቀፉ ገበያ በሚፈልገው ዓይነት በፋብሪካ አቀነባብሮ እሴትን በመጨመር በቀጥታ ለተጠቃሚዎች ፍጆታ ማቅረብ መቻል በዘርፉ በተሻለ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚረዳ ከዓውደ ርዕዩ  ተሞክሮ መገንዘብ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ በዘርፉ የሚታዩ የገበያና የግብይት ችግሮችን ከባለድርሻ አጋራት ጋር በመሆን ለመፍታት በመንቀሳቀስ የንግድ ዘርፉን ለማሳደግ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
 
በዓውደ ርዕዩ ላይ ፈረንሣይ፣ ስፔይን፣ ብራዚል፣ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት፣ ካናዳ፣ ማሊ፣ ሴኔጋልና ሌሎችም በቡና ምርትና ንግድ ግንባር ቀደም ሥፍራን የያዙ አገራትና ኩባንያዎች ተሣትፈዋል፡፡
Algeria02 02.jpgAlgeria03 03.jpg

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከሚያዚያ4-7/2011 ዓ/ም በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው 1ኛው አለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ፎረም እና የንግድ ትርዒት ባዛር ተሳትፎው በሁሉም ንግድ ሥራ ዘርፎች የሚቀርቡ ምርትና አገልግሎቶችን ለጎብኝዎች ማቅረብ ተችሏል፡፡ አንድ የንግድ ተቋምን ለማሳደግና በተሻለ ሁኔታ ቢዝነሱን ለማከናወን እንዲችል የገበያ ልማት ሥራ መሥራት በጣም ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለኮርፖሬሽኑ ጠቃሚ መረጃ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ 

ለሸማች ማህበራት፣ ለአርሶ አደሮች፣ ለጅምላ አከፋፋዮች፣ ለቸርቻሪዎች፣ ለኢንቬስተሮችና ለውጭ ሃገር ተሳታፊዎች ኮርፖሬሽኑን ማስተዋወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በንግድ ትርዒቱ በኮርፖሬሽኑ በተዘጋጀው የቡና ጠጡ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመጋበዝ ኮርፖሬሽኑ ስለተቋቋመበት አላማና በኮርፖሬሽኑ ስለሚቀርቡ ምርትና አገልግሎቶች ዝርዝር ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የተለያዩ የሚዲያ አካላት ስለኮርፖሬሽኑ ዝርዝር መረጃ በአካል ተገኝተው በመጎብኘትና ሰራተኞችን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥተውታል፡፡ የጎብኚዎችን ግብረ መልስ በተመለከተ በተለይ የፍጆታ እቃዎች ለምሳሌ ከውጪ የሚገቡ የዘይት ምርቶች በንግድ ትርዒቶች ላይ ለሽያጭ የሚቀርቡበት ዕድል ቢኖር፤ በፍጆታ እቃዎች ንግድ ሥራ ዘርፍ የሚሠጠው አገልግሎት ለተቋማትና ቲን ቁጥር/ፈቃድ ላላቸው ብቻ የሚከናወን በመሆኑ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የማያደርግ ስለሆነ ይህ አሰራር ቢቀየር፤ እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ በኩል የሚሸጡ ምርቶች የሚሸጡበት ዋጋ ዙሪያ ማስተካከያ ቢደረግ የሚሉ አስተያየቶችና ግብረ መልሶች ተወስደዋል፡፡